ቀጥታ፡

በደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መደወላቡ ዩኒቨርስቲና ብሔራዊ አልኮል ሻምፒዮን ሆኑ

ግንቦት 07 / 2013 (ኢዜአ) የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ የ2013 ዓ.ም ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ፍጻሜውን ሲያገኝ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በወንዶች፤ ብሔራዊ አልኮል በሴቶች ሻምፒዮን ሆነዋል።

በፍጻሜ ጨዋታው በሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ አልኮል ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን በማሸነፍ ሻምፒዮን በመሆን ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሟል።

በዚህ የሴቶች መረብ ኳስ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በትናንት የፍጻሜ ጨዋታ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሻምፒዮን ሆኖ ዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያም ተሸልሟል።

በመደወላቡ የተረታው ወላይታ ድቻ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ፤ ሙገር ሲሚንቶ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ለስፖርቱ እድገት በልዩ ሁኔታ አስተዋጽእ ላበረከቱ አካላትም ሽልማት አበርክቷል።

ለክለቦች አስፈላጊውን ድጋፍ ለሚያደርጉት ለወላይታ ሶዶ እና ለመደወላቡ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶችና ለውድድሩ ስፖንሰር ደርባ ሲሚንቶ ዋና ስራ አስፈጻሚ የስፖርት ትጥቅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ ዘርፎች ለዓመቱ ኮከብ ተጫዋቾችና አሰልጣኞችም የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ በዓመቱ የውድድር ጊዜ ትልቁ ፈተና በኮቪድ-19 ምክንያት ተጫዋቾችን ለማስመርመር የነበረው ወጪ እንደነበረ አስታውሰው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥም የተሳካ ውድድር ማካሄድ መቻሉን ነው የተናገሩት።

ውድድሩ እስከ መጨረሻው ሻምፒዮን የሚሆነው ክለብ ያልለየለት መሆኑ ለክለቦችና ለስፖርት ቤተሰቦች አጓጊ ክስተት እንደነበር ገልጸዋል።

በ2013 የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በወንዶች ሰባት፣ በሴቶች አምስት ክለቦች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም