እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአዊኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍን በመጀመሪያ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአዊኛ ቋንቋና ስነ-ጽሑፍን በመጀመሪያ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር ነው
እንጅባራ፤ ግንቦት 7/2013(ኢዜአ) የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአዊኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሁፍን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የአዊኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሁፍን በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም መጀመር የሚያስችል ዝግጅቱን አጠናቆ የቀረጸውን ሥርዓተ-ትምህርት መገምገሚያ ላይ ከአካባቢው ምሁራንና ከዞኑ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመን ጨምሮ የአዊ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ምሁራን ተሳትፈዋል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው መርሃ-ግብሩን መክፈት የሚያስችለውን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የትምህርት ክፍሉ መከፈት ለአካባቢው ህብረተሰብ ችግር ፈች የተማረ የሰው ሀብት ማፍራት እንደሚያስችልም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ትምህርቱ በመጀመሪያ ዲግሪ በመደበኛና በማታ የትምህርት መርሃ-ግብር የሚከናወን ሲሆን የ4 ዓመት ቆይታ እንዳለውም ተገልጿል።
ሥርዓተ ትምህርቱን ለመቅረጽ የብሔረሰብ ቋንቋዎችን እያስተማሩ ካሉት 5 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ መወሰዱን ጠቅሰው፤“የብሔረሰብ ቋንቋዎችን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እያስተማሩ ካሉ ከሀዋሳ፣ ከአርባ ምንጭ እና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮዎች ተወስዷል” ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ማህበረሰብ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የትምህርት መስኩን መክፈት እንደሚያስፈልግ ቀድሞ መለየቱን ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የጠቆሙት።
መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ በበኩላቸው መርሀ-ግብሩ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ መከፈቱ ቋንቋውን ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲው በቋንቋው የሠለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየተወጣ ያለውን ሃላፊነትም አድንቀዋል።
ቋንቋው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሠጠት የጀመረው በ1989 ዓ.ም ሲሆን የራሱ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ በኮሌጅ ዲፕሎማ ደረጃ የተከፈተው ደግሞ በ2001 ዓ.ም መሆኑን ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዛሬ በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅነት የቀረበው የውይይት መድረክ ነገም በሌሎች ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች እንደሚቀጥል ከዝግጅት መርሀ-ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።