የካውንስሉ መቋቋም ለሃገሪቱ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የካውንስሉ መቋቋም ለሃገሪቱ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ
ሀዋሳ፤ ግንቦት 07/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል መቋቋሙ በሃገሪቱ ለሚከናወኑ የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ።
ካውንስሉ በአዋጅ መቋቋሙ በሀገር ደረጃ ለሠላም እሴት ግንባታ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
በምክክር መድረኩ የካውንስሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ቄስ ዶክተር ዮናስ ይገዙ እንደተናገሩት፤ ካውንስሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመ ነው።
የተለያዩ ወንጌላዊያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናትን በአባልነት ያቀፈው ካውንስሉ በተደራጀ አግባብ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
አብያተ ክርስቲያናቱ በአንድ ማእቀፍ መሰባሰባቸው በክልሉና በሃገሪቱ ለሚከናወኑ የልማትና የሰላም ግንባታ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል።
በተለይ ለረዥም ዓመታት በአብያተ ክርስቲያናቱ ሲነሳ የነበረው ጥያቄ በመንግሥት ምላሽ አግኝቶ ካውንስሉ መመስረቱን ያነሱት ዶክተር ዮናስ፤ በቀጣይ አደረጃጀቱን በክልሎች በማውረድና በዋና ዋና ከተሞች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በመክፈት ስራውን በሙሉ አቅሙ ይጀምራል ብለዋል።
ይህም በተበታተነ መልኩ ይከናወን የነበረው የአብያተ ክርስቲያናቱ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች በተደራጀ አሰራር ለማከናወን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄነራል በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው፤ ለሃይማኖት ተቋማት የህጋዊ ሰውነት እውቅና መሰጠቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረው፤ የእምነቱ ተከታዮች አደረጃጀቱን ተጠቅመው ሐይማኖታዊ ተልዕኳቸውን ከማከናወን ባለፈ የመንግስት አጋዥነታቸውን በህጋዊ መልኩ ለማከናወን እንደሚያስችላቸውም ጠቅሰዋል።
በርካታ ተከታቶች ያሏቸው የእምነት ተቋማት በአንድ ዓላማ መሰባሰባቸው ሰላምንና አብሮነትን በየደረጃው ለማጎልበት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ድርሻቸው የጎላ እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ በሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የሃይማትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ደብሪቱ ዳሪሞ ናቸው።
በሌሎችም ሃገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከካውንስሉ ጋር በቅርበት ለመስራት እቅድ መንደፋቸውንም ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ከበደ ፎገራ በበኩላቸው ፤በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ወንጌላዊያን አማኞች መንግስት በሚያካሂደው የልማት ተግባራትና በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ካውንስሉ በአዋጅ መቋቋሙ አባላቱ ኃላፊነታቸውን በተሻለ አሰራር በመደገፍ ለሀገሪቱ ህዳሴ ጉዞ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያግዛልም ነው ያሉት።
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ከፌዴራልና ሲዳማ ክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ ካውንስሉ የተቋቋመበት አዋጅ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ግንዛቤ ገለጻ ተደርጓል።