ቀጥታ፡

ጣቢያው ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃዎችን ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ያደርጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 07 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ያስገነባው የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ የሳተላይት መረጃዎችን ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ አስታወቀ።

ጣቢያው ከአምስት የቻይና ሳተላይቶች መረጃዎችን እንደሚቀበልም ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ዶክተር አህመዲና መሐመድ እና ዶክተር ፎዚያ አሚን፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ማዕከሉን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።

ሦስት ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተደረገበትና 7 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ ያለው የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ፈጅቷል።

በቻይናው 'ሄድ ኤንድ ክሬሴዳ ኮንሰርቲየም' ኩባንያ የተገነባው ጣቢያ ሙሉ ወጪ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑ ተገልጿል።

ጣቢያው የሳተላይት መረጃዎችን የማከማቸት፣ የመተንተንና ወደ ምስል የመለወጥ ስራ የሚከውን ሲሆን ከመሬት ምልከታ ሳተላይቶች እስከ 0 ነጥብ 5 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ መቀበል ይችላል ተብሏል።

የጣቢያው ዓላማ የኢትዮጵያን የሳተላይት መረጃ አጠቃቀም ማሳደግና መረጃዎቹን አገሪቷ ለልማት ሥራዎች እንድትጠቀም ማስቻል መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ጣቢያው የሚቀበላቸውን የሳተላይት መረጃዎች ለጎረቤት አገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚያስችል ገልጸው፤ የአገር ውስጥ ተቋማት የሳተላይት መረጃዎችን ለማግኘት የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀርም አመልክተዋል።

ጣቢያው ጋኦፈን-1፣ ጋኦፈን-3፣ ጋኦፈን-5፣ ሲ.ቢ.ኢ.አር.ኤስ-4 እና ሱፐርቪው-1 ከተባሉ የቻይና ዓለም አቀፍ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መረጃዎችን ከ15 ደቂቃ እስከ አንድ ሠዓት ባለው ጊዜ እንደሚቀበል አስረድተዋል።

"በቀጣይም ከበርካታ ሳተላይቶች ጣቢያው መረጃ እንዲቀበል የማድረግ ዕቅድ አለ፤ ለዚህም የሚያግዝ የአቅም ማጎልበት ሥራ ይከናወናል" ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በበኩላቸው "የጣቢያው ግንባታ የሳተላይት መረጃዎች ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማጎልበትና የሰለጠነ የሰው ሃይል ለመጨመር ወሳኝ ሚና አለው" ብለዋል።

ከጎረቤት አገሮች ጋር በዘርፉ ያለውን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጎለበትም ነው የገለጹት።

የቻይና ሄድ ኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዌይ ሱን ኩባንያቸው ኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስ እያስመዘገበች ያለውን እድገት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

"የጣቢያው ግንባታ ኩባንያውና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የረጅም ጊዜ ትብብር ጅማሬ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ከብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ምርቃት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የቻይና ሄድ ኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ኩባንያ በሕዋ ሳይንስና ተያያዥ ጉዳዮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም በታሪኳ የመጀመሪያውን ETRSS-01 የተሰኘችውን ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ መላኳ የሚታወስ ነው።

በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም ደግሞ ET-Smart-RSS የተሰኘችውን ሁለተኛዋን ሳተላይት በተመሳሳይ ከቻይና ወደ ሕዋ አምጥቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም