ቀጥታ፡

"በየትኛውም አካል የተከፈተብን ዘመቻ ሳይበግረን ሪቫን እየቆረጥን ኢትዮጵያን እናሻግራታለን" - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ

ግንቦት 07 ቀን 2013 (ኢዜአ) በየትኛውም አካል የተከፈተብን ዘመቻ ሳይበግረን ተስፋ ሳይሆን ሪቫን እየቆረጥን ኢትዮጵያን እናሻግራታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በአፋር ክልል የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን መርቀው ሲከፍቱ ነው።

የአፋር ክልል የኢትዮጵያ ብልጽግና ከሚረጋገጥባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


በንግግራቸው በንዋይ ብዛት የሚያስቡ አገሮችም ሆኑ አካላት ኢትዮጵያዊያን እንዴት መኖር እንዳለባቸው እኛ ካልወሰንን በሚል ዘመቻ ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ለመልማት ያለን ፍላጎት በሌሎች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በእኛው የሚወሰን እንደመሆኑ ተስፋ ባለመቁረጥ ልንበረታ ይገባልም ብለዋል።

ታሪካችን የሚያስተምረን ኢትዮጵያዊያን በማንም ተጽዕኖ ውስጥ እንዳልወደቁና ወደፊትም እንደማይወድቁ ነውም ብለዋል።

በመሆኑም የትኛውም ፈተና ሳይበግረን ተስፋ ሳይሆን ሪቫን እየቆረጥን የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ብሩህ እናደርገዋለን ብለዋል።

ኢትጵያዊነት ማለት ነጻነት እና ክብር መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'እኛ ኢትዮጵያዊያን በቅኝ ያልተገዛንና የማንገዛ፤ ያልተንበረከክንና የማንንበረከክ ሕዝቦች ነን" ነው ያሉት።

የየትኛውንም አገር የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሀሳብ ሳንቀበል ብልጽግናችንን እውን እያደረግን እንቀጥላለን ብለዋል።

የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቀጣይ አገሪቱ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለምታከናውናቸው ተግባራት ፈር ቀዳጅ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም በሁሉም ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሪቫን እየቆረጥን ለዓለም ኢትዮጵያዊነት ማለት ነጻነት እና ክብር መሆኑን እናረጋግጣለን ብለዋል።

የአፋር ክልል ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም ለአገር ውስጥ ፍላጎትም ይሁን የዓለም ገበያን ለመድረስ ፓርኩ ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የምናደርገውን ጥረት ማንም አያስቆመንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ምርጫውን ለማካሄድም የማንንም ፈቃድ አንጠይቅም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም