ቀጥታ፡

በኮምቦልቻ የተገነባው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ ተመረቀ

ደሴ ፤ ግንቦት 07 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በኮምቦልቻ አየር መንገድ በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስነባውን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ (ታወር) ዛሬ አስመረቀ።

በምረቃው ስነ-ስርዓት የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ጀነራል ተወካይ አቶ ፍቃዱ ውለታው እንደገለጹት፤ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተገነባው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ የአውሮፕላኖችን እንቅስቃሴ በመከታተል ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ያስችላል።

"የባለስልጣኑና የአየር መንገዱ ባለሙያዎች ከዚህ በፊት በሬድዮ መገናኛ ብቻ ይገናኙ ነበር" ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ የማማው መገንባት የግንኙነት መረቡን እንደሚያዘምነው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአየር ንብረቱን በቀላሉ ለመረዳትና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ቃለአብ በበኩላቸው፤ በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ ለመጣው የአየር መንገዱ ተጠቃሚዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ማማው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ በኮምቦልቻ በቀን ሦስት በረራዎች ያሉት ሲሆን ከ240 በላይ ሰዎችን እንደሚያጓጉዝ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ እንዳሉት፤ ለአየር መንገዱ ስራ መቃናት የዞኑ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ ነው፡፡

የአቪየሽን ባለስልጣኑና አየር መንገዱ በዳመና ጊዜ የሚስተዋለውን መጉላላትና ያለውን የተርሚናል እጥረት በማቃለል የኢንዱስትሪ ፓርኩና ፋብሪካዎች ምርት በቀላሉ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

አየር መንገዱ ለሚያቀርበው የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዞኑ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም