ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ከስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ እየተዘጋጀ ነው

ጋምቤላ፤ ግንቦት 07/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መረሃ ግብር የሚውል ከስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ባለፈው ክረምት ከተተከለው ችግኝ 82 በመቶ መጽደቁም ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል ለኢዜአ እንዳሉት፤ እየተዘጋጀ ያለው ችግኝ  በክልሉ 13 ወረዳዎች በተቋቋሙ 65 የችግኝ ጣቢያዎች ነው።

እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ ልማት መረሃ ግብር እቅድ የክልሉ ድርሻ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ችግኝ ቢሆንም ከእቅዱ በላይ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እየተዘጋጀ ከሚገኘው ችግኝ ውስጥ የሎሚ፣ ማንጎ፣ ፓፓያን ጨምሮ 80 በመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና የአካባቢው የዛፍ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም  የህብረተሰቡን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግና የአካባቢ የዛፍ ዝርያዎች እንዳይጠፉ በማሰብ ነው ብለዋል።

ባለፈው ክረምት በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ ልማት  መረሃ ግብር በተራቆቱ አካባቢዎች ከተተከለው አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ችግኝ መካከል  82 በመቶ  በተደረገለት እንክብካቤ ማጽደቅ መቻሉን ኃላፊው አመልክተዋል።

ዘንድሮ ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ተከላ ያለውን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ የባለሙያዎች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ኬት ቾል ናቸው።

እየተዘጋጀ ያለው ችግኝ በበጋው ወራት የተፋሰስ ልማት በተሰራባቸውና ከሰው ንክኪ በተከለሉ ቦታዎች እንደሚተከሉ ጠቁመው ከግንቦት 20/2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተከላ ቦታ ዝግጅት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም