የምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ከተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚራዘም ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ከተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚራዘም ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 07 /2013 (ኢዜአ) የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ መስጫ በተያዘለት ቀን እንደማይካሔድና እስከ ሶስት ሳምንት የሚደርስ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ድምጽ መስጫ ቀን ከሌሎች አካባቢዎች ጋር በአንድ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ ባጋጠሙ ችግሮችና በተወሰዱ መፍትሄዎች እንዲሁም የድምጽ መስጫ ቀን ማራዘምን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መክሯል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሄዎች እንዲሁም የድምጽ መስጫ ቀን በተቀመጠለት ጊዜ ለማካሄድ ያሉ ክፍተቶችን አብራርተዋል።
እስካለፈው ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከ36 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመራጭነት መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በበርካታ ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ መጀመርና ሌሎች ችግሮች ምዝገባው በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ቦርዱ ለድምጽ መስጫ ቀን የሚያስፈልጉ ቀሪ ሥራዎችን በቀሪ ቀናት ማከናወን ባለመቻሉ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረውን ድምጽ የመስጠት ሂደት እንደሚራዘም ገልጸዋል።
በመሆኑም ቦርዱ ካስቀመጠው የድምጽ መስጫ ቀን ቢያንስ ሁለትና ሦስት ተጨማሪ ሳምንታት እንደሚያስፈልገው ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የምርጫውን አፈጻጸምና የሥራ ጫና ለማቃለል ድምጽ የመስጠት ሂደቱ ሰኔ 5 ቀን እንዲሆን ተወስኖ እንደነበር አውስተዋል።
ይሁን እንጂ ሂደቱ ከፓለቲካ ፓርቲዎች በኩል ጥርጣሬ በመፍጠሩ የነበረውን ቅሬታ በመቀበል ምርጫው በሁሉም የአገሪቱ አካካቢዎች በአንድ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑን ወይዘሪት ብርቱካን አስረድተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው በመራጮች ምዝገባ ወቅት የግልጸኝነት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ምቹ አለመሆንና ሌሎች ችግሮችን ዘርዝረዋል።
የድምጽ መስጫ ቀን ባሉት ችግሮች ምክንያት መራዘሙ አሳማኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሱ ሃሳቦችን በማካተት በቀጣይ የምርጫውን ድምጽ መስጫ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አስታውቀዋል።