ቀጥታ፡

የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 07 ቀን 2013 (ኢዜአ) የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ምረቃ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ተከናወነ።

የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያው ግንባታ የተከናወነው በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ነው፡፡

ጣቢያውን ለመገንባት ሁለት ዓመት የወሰደ ሲሆን ሦስት ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጎበታል፤ ወጪው ሙሉ በሙሉ በመንግስት ነው የተሸፈነው።

የሳተላይት መረጃ ፍላጎትን በዓይነት፣ በጥራትና በመጠን በማሟላት መረጃው ለተለያዩ የልማት ተግባራት እንዲውል የሚያስችለው ጣቢያው 7 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ እንዳለው ተነግሯል፡፡

የጣቢያው መገንባት በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ለሳተላይት መረጃ የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀር ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ በተበታተነ መልኩ የሚገኘው የሳተላይት መረጃ በአንድ ማዕከል እንዲሆን ያስችላል ተብሏል።

ሳተላይት ካላቸው አገሮች ጋር በነጻና በትብብር የውል ስምምነት በመፈጸም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የሳተላይት መረጃዎችን መጠቀም እንደሚያስችልም ተነግሯል።

ጣቢያውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሣ ይልማና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዎች ዶክተር አህመዲን መሃመድ እና ዶክተር ፎዚያ አሚን መርቀውታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም