ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገር አቀፍ የሕጻናት የሳይንስና የፈጠራ መርሃ ግብር እያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ

ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕጻናት በሳይንስና ፈጠራ ያላቸውን ክህሎት ያሳድጋል ያለውን አገር አቀፍ መርሃ ግብር እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያዘጋጀ ያለውን መርሃ ግብር አስመልክቶ የመጀመሪያው የግብአት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

አገር አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ መርሃ ግብር ሀሳብ የተጠነሰሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስን ተደራሽ የሚያደርግ የቴሌቪዥን መርሃ ግብር እንዲያዘጋጅ በመንግስት በተሰጠው መመሪያ አማካኝነት ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ ልጆች በሳይንስና በፈጠራ የተካኑ ሆነው እንዲያድጉና ብሎም የዓለም ችግሮች መፍታት እንዲችሉ እድል መፍጠርና አውዱን ማመቻቸት የመርሃ ግብሩ ዋንኛ አላማ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን የሳይንስ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ቁጥር የማሳደግ ፋይዳ አለው ተብሏል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የሳይንስ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ከመደርደሪያ ባለፈ የማህበረሰቡን ችግር መፍታት ያልቻሉት በዜጎች ላይ የሳይንስ እሳቤ ማስረጽ ባለመቻሉ ምክንያት ነው ብለዋል።

ማህበረሰቡ ሳይንስን ለእድገትና ለለውጥ ይሆነኛል ብሎ ካልተቀበለው በስተቀር በአንድ አገር ውስጥ ሳይንስና ፈጠራ ሊያድግ እንደማይችል አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ሳይንስን ወደ ሕብረተሰቡ ለማስረጽ ከታች ጀምሮ ሳይንስን ተቀብሎ የሚያድግ ዜጋ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም በሕጻናት ላይ መስራት ወሳኝ እንደሆነና መርሃ ግብሩም ከዚህ አንጻር እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ነው ፕሮፌሰር ጣሰው ያስረዱት።

ለመርሃ ግብሩ ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲዲቲ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አበባው ፍቃዱ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ የሳይንስና የፈጠራ እድገት ዘላቂነት እንዲኖረው አገር በቀል የእውቀት ሽግግርን መንገዶችን ለመጠቀም ምቻ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ እንደታመነበት አመልክተዋል።

አገር አቀፍ የሳይንስና የፈጠራ መርሃ ግብሩ በመነሻነት ለአምስት ዓመት ተግባራዊ በማድረግና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩን በመጀመሪያ በሙከራ በቀጣይ ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባ መሆኑንና ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልግ ሀብት ከአገር ውስጥና ከውጭ ለማሳበሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩን የሚያስፈጽም የፕሮጀክት ቢሮ እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር፣የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት የመርሃ ግብሩ አስፈጻሚ እንደሚሆኑም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም አካዳሚው በመርሃ ግብሩ አማካኝነት የሳይንስና ባህል ከሕጻናት ለመጀመር ለሚከናወነው ስራ ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።


በመርሃ ግብሩ የሕጻናትን የእድሜና የእድገት ደረጃ ባማከለ መልኩ ቢዳብር እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን መጠቀም የመርሃ ግብሩ ሀሳብ እንዲሸጥ እንደሚያደርገው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

በተጨማሪም ለሕጻናት ሁለንተናዊ እድገት ሳይንስ ወሳኝ መሆኑንና ለዚህም የሚያስፈልገውን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በበኩላቸው መንግስት ለመርሃ ግብሩ ተፈጻሚነት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱና የቅንጅት አሰራሩ ጠንካራ ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

አገር አቀፍ የሳይንስና ፈጠራ መርሃ ግብር ግብአትና ምክረ ሀሳቦች የሚሰበሰቡባቸው ተከታታይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም