ቀጥታ፡

እድሮች ለአገር ሠላምና ብልጽግና ያላቸውን ሚና እንዲያጠናከሩ ተጠየቀ

ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) እድሮች ለሀገር ሠላምና ብልጽግና ያላቸውን ሚና እንዲያጠናከሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከከተማዋ የእድሮች ምክር ቤት ጋር በመሆን "እድሮች ለሀገር ሠላምና ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ ዓመታዊ የእድሮች ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡

በንቅናቄ መርሃ-ግብሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ፣ የእድሮች ምክር ቤት የቦርድ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ እድሮች የአብሮነት፣ የአንድነትና የመተባበር ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እድሮች ቋንቋና ብሔር ሳይገድባቸው ሁሉን በማሳተፍ የአብሮነት ጥንካሬ እንዲጎለብት የማይተካ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አውስተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተግዳሮት በሆነበት ጊዜ እድሮች አገራዊ ጥሪ በመቀበል ከማዕድ ማጋራት ጀምሮ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱም አስታውሰዋል።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታና ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማድረግ፣ በአካባቢ ጽዳትና ሌሎች ማኅበራዊ ክዋኔዎች በመሳተፍ ከፍያለ አበርክቶ ካደረጉ ተቋማት እድሮች ተጠቃሽ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

ምክትል ከንቲባዋ እድሮች አሁነም ለአገር ሠላምና ብልጽግና እንዲሁም ትብብር ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው እድሮች በከፍተኛ ሁኔታ ከሚሳተፉባቸው አገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጠቅሰዋል።

እድሮች አባላቶቻቸውን በማስተባባር ለግድቡ ግንባታ ያደረጉት ድጋፍ ዘንድ ዘመን ተሸጋሪ ሆነውን የማኅበረሰቡን የመረዳዳት ባህል ይበልጥ ማጉላቱንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ እድሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት ገብረማርያም እድሮች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከልን ጨምሮ እያከናወኗቸው ያሉ ሌሎች ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ ለአዲስ አበባ እድሮች ምክር ቤት አባላት ስልጠናና የተለያዩ ድጋፎች ላበረከቱ 14 ተቋማት ዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም