ቀጥታ፡

ፅህፈት ቤቱ ከ1 ሺህ 500 ለሚልቁ የፈጠራ ውጤቶች ጥበቃ አድርጓል

ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ባለፉት 9 ወራት ለ1 ሺህ 658 የፈጠራ ውጤቶች ጥበቃ ማደረጉን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ዓለም አቀፉን የአእምሯዊ ንብረት ቀንአስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን አበይት ስራዎች የሚዳስስ ሰነድ ለውይይት አቅርቧል።

ጥበቃ የተደረገላቸው "የንግድ ምልክት፣ፓተንት፣ ግልጋሎት ሞዴል፣ አስገቢ ፓተንት፣ ኢንዱስትሪያል ንድፍ እና የቅጅ መብቶች ናቸው።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሀን የአእምሯዊ የፈጠራ ውጤቶችን በመመዝገብ የፈጠራ ባለቤቶች ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአእምሯዊ ንብረት ቀን በኢትዮጵያ መከበሩ ሰዎች ስለ አእምሯዊ ንብረት ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ እገዛ እንደሚያደርግም አንስተዋል።

ጽህፈት ቤቱ የአእምሯዊ ንብረቶችን ከመጠበቅ ጎን ለጎን በተያዘው ዓመት ከአገልግሎት ክፍያ 18 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ፓተንት ላይ የደረሱ ስራዎች በጣም ዝቅተኛ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች ወደፓተንት ደረጃ እስከሚያድጉ "ግልጋሎት ሞዴል" በሚል ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በዘርፉ  የትምህርት ማዕከል ለመገንባት የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጽህፈት ቤቱ ከክልሎች ጋር በመሆን ለፈጠራ ስራዎች የጥበቃ አገልግሎት ለመስጠት ስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ኤርምያስ ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ለጽህፈት ቤቱ ከቀረቡ 429 ቅሬታዎች  መካከል 416 ለሚሆኑት ምላሽ መሰጠቱን ገልጸዋል።

እንዲሁም ባለ ልዩ ጣእም የግብርና ምርቶች በወል ንግድ ተመዝግበው አምራቾች ከምርቶቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋቱንም አንስተዋል።

የአእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በአዋጅ ከተቋቋመበት 1996 ዓ.ም ጀምሮ ለ18 ሺህ 895 የፈጠራ ውጤቶች ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

21ኛው ዓለም ዓቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀን በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም