ቀጥታ፡

የሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሩ የሠራዊቱን አባላት በዓለምአቀፍ መስፈርቶች ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው

ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) የዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በቅርቡ የሚጀምረው የሠላምና ግጭት አፈታት የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብር የሠራዊቱን አባላት በዓለምአቀፍ መስፈርቶች ብቁና ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚሰማሩ ወታደሮች ሙያዊ ብቃታቸው የተረጋገጠና የአገራቸውን ክብር የሚያስቀድሙ ሊሆኑ እንደሚገባም ተገልጿል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የዓለምአቀፍ ሠላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት 'በሠላም እና ግጭት አፈታት' የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ-ግብር ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚጀመር ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ በአዲሱ ስርዓተ-ትምህርት ላይ ከመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

የኢንስቲትዩቱ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ያካበተችውን የረጅም ጊዜ ተሳትፎና ልምድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች በሁሉም ግዳጆች ያለምንም መዋዠቅ ተልዕኳቸውን በብቃት በመወጣታቸው በአንዳንድ ግዳጆች ብቸኛ ተመራጭ ሆነው እንዲሰማሩ መደረጉንም አውስተዋል።

ብርጋዴር ጄኔራሉ ሠራዊቱ በሚሰማራባቸው አንዳንድ ተልዕኮዎች ከሚያጋጥሙ ክፍተቶች የቋንቋ ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ታምራት አንዳርጌ በበኩላቸው ሠራዊቱ ያሉበትን እጥረቶች ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ 'በሠላም እና ግጭት አፈታት' የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ-ግብር ለማስጀመር በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።

ይህም በተለይ በዘርፉ ተልዕኮ የሚሰጣቸው የሠራዊቱ አባላት በየትኛውም ቦታ ሲሰማሩ ብቁና ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

በአገር መከላከያ የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ተቋማት አሰራራቸውን ከዘልማድ ወደ ሙያዊና ሳይንሳዊ እየቀየሩ መሆኑን ገልፀዋል።

መከላከያም እንዲሁ ከተቋማዊ አደረጃጀት ጀምሮ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ነው የተናገሩት።  

ኢትዮጵያ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ስትሳተፍ መቆየቷን አስታውሰው 'ከተልዕኮው የተገኘው ትርፍ ወታደሮቿ ያከናወኑት የዲፕሎማሲ ሥራ ነው' ብለዋል።

አሁንም በዓለምአቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ብቃት ያለው ወታደር መፍጠ ይገባል ነው ያሉት።

ዓለምአቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚወስዱ ወታደሮች ለአገር ክብር ቅድሚያ በመስጠት ጥቅማቸውን ማስከበር እንዳለባቸውም አንስተዋል።

'በሠላም እና ግጭት አፈታት' የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ-ግብር የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ከሁለት ወራት በኋላ ይጀመራል ተብሏል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1948 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ወታደሮችን ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ማሰማራቷን መረጃዎች ያሳያሉ።

እ.አ.አ ከ1951 እስከ 2021 በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ፣ በሱዳን ዳርፉር፣ በአብዬ፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ከ140 ሺህ በላይ ሠላም አስከባሪ ወታደሮቿን ማሰማራቷን የኢንስቲትቱ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም