የኢትዮጵያ የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ተመሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ተመሠረተ
ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር በቱሪዝም ዘርፍ የጋዜጠኝነት ሙያን ለማሳደግና የዘርፉን አቅም ለማጎልበት እሰራለሁ አለ።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም እንደተናገረው፤ የአገሪቱ የባሕልና የቱሪዝም ኃብት የሚጠበቀውን ያህል አልተዋወቀም።
በዚህ ሳቢያም የባሕል ትውውቅ ማጎልበት፣ በኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቆይታ ማጠናከርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ አልተቻለም።
ችግሩን ለመቅረፍ በማሰብ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተለይም በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ተሰባሰበው ማኅበሩ መመሥረቱን ነው የገለጸው።
ማኅበሩ በዋነኝነት በአገሪቱ የቱሪዝም ጋዜጠኝነትን ጽንሰ ሃሳብ ለማሳደግና አቅም ለማዳበር እንደሚሰራ ጋዜጠኛ ሄኖክ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው የዘርፉ ጋዜጠኞች የቱሪዝም ዘርፉን ለመደገፍ መደራጀታቸውን አድንቀዋል።
የዘርፉን እድገት የሚመራው መረጃ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ የዘርፉ ጋዜጠኞች ለቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ማኅበሩ የቱሪዝም መስህቦችን በማስተዋወቅ፣ ግንዛቤ በመፍጠርና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ያለበትን አገራዊ ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣም ጠይቀዋል።
ማኅበሩ ለቀድሞዋ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አዳነኝ ዳሌቾ ለማኅበሩ ምሥረታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥቷል።
አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የባሕልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር 30 አባላት እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።