የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር ፈቺነት እንዲያረጋግጡ ለማስቻል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር ፈቺነት እንዲያረጋግጡ ለማስቻል እየተሰራ ነው
ሆሳዕና ፤ ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር ፈቺነት በተግባር እንዲያረጋግጡ ለማስቻለ እየተሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ተቋማት ሚኒስቴር ገለጸ።
’’ፍላጎት ተኮር ምርምር ለማህበረሰቡ ችግር መፍትሄ ’’በሚል መርህ የተዘጋጀው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ዛሬ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።
በሚኒስቴሩ የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር በወቅቱ እንዳሉት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተሰጣቸው ተልዕኮ አንዱ ጥራት ያለው ምርምር በማድረግ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማድረስ ነው።
ይህ እውን እንዲሆን ሚኒስቴሩ በምርምርና በተለያየ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ በሀገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን አስተዋጽኦ ከፍ እንዲያደርጉ የተለያየ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እየደገፈ መሆኑን አመልክተዋል።
በሂደት የሚገጥሙ ችግሮች ለመፍታት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የተሻለ የምርምር ስራዎች እንዲካሄዱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን ከይስሙላነት ባለፈ ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተመራማሪው ጀምሮ ውጤቱን ሰርቶ ለሚያባዛው አካል ተደራሽ በማድረግ በኩል የሚስተዋሉ ችግሮች እንደ ሀገር ውስንነት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ለማቃለል በአካባቢ ማህበረሰብ ችግር ፈቺ ምርምር ዘርፍ ለግብርና፣ ማኒፋክቸሪንግ፣ አይሲቲ ፣ ቱሪዝምና ማይኒንግ የፕሮፌሰሮች ካውንስል በማቋቋም ምርምር እንዲካሄድ ሚኒስቴሩ ትኩረት በመስጠት ለተግባራዊነት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አመልክተዋል
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸሰቀ ላምቦሬ በበኩላቸው ፤ በተያዘው ዓመት በተቋሙ የማህበረሰቡን ችግር በመለየት 129 ምርምሮች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።
በምርምሩ ከተገኙት ውስጥ የተመረጡ 21 ውጤቶች ለኮንፍረሱ መቅረቡን ጠቁመው ፋይዳቸው ታይቶ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሰቲው የአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት በማድረግ ከማህበራዊ ዘርፍ በተጨማሪ በሰባት ምርምር ማዕከላት በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ለግብርናና መዳሐኒትንት በሚጠቅሙ እጽዋት፣ የደጋ ፍራፍሬና አካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እስካሁን በተደረገው ጥረት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮንፈረንሱ በምርምር ዘርፍ ብቁ የሆኑ ምሁራን ተሞክሮዎችን ለሌሎች በማካፈል ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡
ከኮንፍረንሱ ተካፋዮች መካከል የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ በፍቃዱ መውደድ ፤ ተቋሙ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የብዝሀ ህይወት ሀብቶችን የመጠበቅና ለዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ለማስቻለ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኮንፍረንስ ከምሁራን የሚገኘውን እውቀት በመጠቀም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ጥራት ያለው ምርምር ለማካሄድ ልምድ የሚቀሰምበት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው ኮንፍረንስ ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ የጥናትና ምርምር ምሁራንና ምርምር ተቋማት ወኪሎች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።