በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ በምርምር የታገዘ የጥናት ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው

ጎንደር ግንቦት 06/2013 ሶስት አለም አቀፍ ድርጅቶች በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚገኙትን ብርቅዬ የዱር እንስሳትና የብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅ በምርምር የታገዘ የጥናት ፕሮጀክት እያካሄዱ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

 የፓርኩን ወቅታዊ የዱር እንስሳት ሀብት ቁጥር መረጃ ለማደራጀትም የቆጠራ ስራ በቅርቡ መካሄዱ ተመልክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአለም አቀፍ ድርጅቶቹ ጥናትና ምርምሮች ትኩረት ያደረጉት በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኙት ዋልያ ፣ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ ነው፡፡

ከአራት እስከ 15 ዓመታት ቆይታ ያላቸውን የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶችን በፓርኩ ክልል ውስጥ እያከናወኑ የሚገኙት ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ፣ አፍሪካን ዋይልድ ላይፍና ደብሊው ሲፒ የተባሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በፓርኩ ክልል ለ15 ዓመታት የሚዘልቅ በጭላዳ ዝንጀሮ የአኗኗር የአመጋገብ የስነ-ተዋልዶ ባህሪና ዝርያ እንዲሁም የጤና ስርዓትና የበሽታ ስርጭት ጥናትና ምርምር እያካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ደብሊው ቢሲ የተባለው የቀይ ቀበሮ ጥበቃ ድርጅት በበኩሉ ፤በፓርኩ ክልል የሚገኙ ቀይ ቀበሮዎችን ከእብድ ውሻ በሽታ ለመጠበቅ የሚያስችል የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ድርጅቱ ከውሾች ወደ ቀይ ቀበሮዎች የሚተላለፈውን የእብድ ውሻ በሽታ ለመከላከል የቀይ ቀበሮዎች ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዙ ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ፡፡

በተጨማሪም በቀይ ቀበሮዎች መኖሪያዎች አካባቢ በስነ-ተዋልዶ በአመጋገብና በጤና ሁኔታ ዙሪያም ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ነድፎ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የፓርኩን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅና የብዝሃ ሕወቱን የአደጋ ስጋት ለመቀነስ የአራት ዓመታት ፕሮጀክቶችን ነድፎ በጥናትና ምርምር እየደገፈ የሚገኘው አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ የተባለ ድርጅት ነው፡፡

ድርጅቱ ፓርኩን የማኔጅመንት ፕላን ከማዘጋጀት ጀምሮ የፓርኩን የእሳት አደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ፕሮጀክት እያካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ 

የፓርኩን ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ አኳያም ተስማሚ ሀገር በቀል የደን ዛፍ ዝርያዎችን በምርምር ከማቅረብ ጀምሮ የፓርኩን መሰረተ ልማት ለማዘመን የሚያግዙ ሳይንሳዊ ድጋፎችን እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡

የፓርኩን የብርቅዬ የዱር እንስሳት ሀብት ቁጥር በጥናትና መረጃ ለማስደገፍ ባለፈው ወር መጨረሻ የዋልያዎች የቆጠራ ስራ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ የፓርኩ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ናቸው፡

የቆጠራውን ውጤት በቅርቡ ይፋ ለማድረግ በዘርፉ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎችና ቴክኖሎጂ በመደገፍ የመረጃ ትንተና እና ማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

እንደአውሮፓ አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት / ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

በድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥ የታደለው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም