የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቻይና ሕዝብ ነጻነት ጦር የፀረ ኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቻይና ሕዝብ ነጻነት ጦር የፀረ ኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ ተደረገለት
ግንቦት 6/2013 (ኢዜአ) የቻይና ሕዝብ ነጻነት ጦር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፀረ ኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ አበረከተ።
ድጋፉን የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በኢትዮጵያ ከቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢውሃን ተረክበዋል።
አምባሳደር ዣዎ ዢውሃን እንዳሉት ከቻይና ነጻነት ጦር የተሰጠው ጸረ ኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ የሁለቱ እህትማማች አገራትና የጦር ሠራዊቶች ጥብቅ ግንኙንት እንዳላቻው አብነት ነው።
የቻይና ጦር ሃይል ከወረርሽኙ መነሻ ጀምሮ ለመከላከል ከባድ ፈተናዎችን ማለፉን ገልጸው፤ ለኢትዮጵያ መከላከያ የተደረገው ድጋፍም የጦሩ አባላትና መኮንኖችን ከወረርሽኙ ለመታደግ እንደሚያግዝ አክለዋል።
በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሃይቴክ ሆስፒታል ግንባታን እንደሚደግፍና በሌሎች የትብብር ዘርፎችም በቅርበት እተየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ቅርብ ወዳጅና ታማኝ ጓደኛም የቻይና ሕዝብ ነጻነት ጦር ኮቪድ-19ን ለመከላከል ድጋፉን ያጠናክራል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያና ቻይና ጦር ሃይሎች የትብብር መስክ መጠነ ሰፊ መሆኑን ገልጸው፤ ወደፊትም በሚደረጉ ስምምነቶች ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብሮች እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ በበኩላቸው የቀደምት ስልጣኔ ባለቤቶቹ ኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ዘመን ወዳጅነት ያላቸው በተለይም ከ50 ዓመታት ወዲህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ የመጡ ወዳጆች ናቸው ብለዋል።
በዚህም ከኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በተጨማሪ ወታደራዊ ትብብራቸውም ጠንካራ መሆኑን አንስተዋል።
ለአብነትም ቻይና ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል፣ በቢሾፍቱ ለሚገነባው የሃይቴክ ሆስፒታል ድጋፍ እያደረገች መሆኗና በጦር ሃይሎች ሆስፒታልም የባለሙያ እገዛዋን አንስተዋል።
ዶክተር ቀነዓ ለተበረከተው የፀረ ኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍም አመስግነዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በወቅታዊ ሁኔታ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ለምታደርገው ጥረት ቻይና በጸጥታው ምክር ቤት ያሳየችው የኢትዮጵያ ወገንተኝነት አድንቀው፤ ለዚህም ምስጋና ችረዋል።
ከፀረ ኮቪድ-19 ክትባት በተጨማሪም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈርሟል።