የኢትዮጵያና ቻይና የዲፕሎማቲክ ግንኙነት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ቴምብሮች ታተሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ቻይና የዲፕሎማቲክ ግንኙነት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ቴምብሮች ታተሙ
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያና ቻይና የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ለተመሠረተበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ የተዘጋጁ ሁለት ቴምብሮች ታትመው ዛሬ ለሽያጭ ቀርበዋል።
ቴምብሮቹን የኢትዮጵያና የቻይና ፖስታ አገልግሎቶች አጋርነት በመፍጠር የአገራቱን 50ኛ ዓመት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በሚያሳይ መልኩ ማዘጋጀታቸው ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራአስፈፃሚ ሃና አርያስላሴ፣ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የሚኒስትር አማካሪና ምክትል ሃላፊ ዣ ታያን እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ቴምብሮቹ ተመርቀዋል።
ዋና ስራአስፈፃሚዋ ኢትዮጵያና ቻይና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ላይ የተመሰረት ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በእኩልነት፣ በመከባበርና መደጋገፍ ላይ የተመሰረት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅማቸውን ያስጠበቀ እንደሆም ገልፀዋል።
በቴምብሮቹ ላይ የቻይና አሻራ ያረፈበት የወዳጅነት ፓርክ እና ለ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ የተገነባው የቤጂንግ ኦሎምፒክ ጫካ ፓርክ ምስሎች መካተታቸውን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የሚኒስትር አማካርና ምክትል ሃላፊ ዣ ታያን በበኩላቸው የቴምብሮቹ መታተም የሁለቱን ወንድማማች አገራት ግንኙነት ያጠናከረ ነው ብለዋል።
በቴምብሮቹ ላይ ያረፉት ምስሎች የኢትዮጵያ እና ቻይናን የረጅም ጊዜና እያደገ የሚሄደውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያንፀባርቁ እንደሆኑም ገልፀዋል።
ቴምብሮቹ በሁለቱ አገራት ለሚገኙ ዜጎች እንደሚሰራጩና የአገራቱም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ቴምብሮቹ በወጡበት ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤትና በተመረጡ ቅርንጫፎች ለሽያጭ መቅረባቸው ተገልጿል።