አሜሪካዊቷ የ26 ሚሊዮን ዶላር የሎቶሪ አሸናፊ ቲኬት ከልብስ ጋር አጠበች

109

ግንቦት 6 ቀን 2013ዓ.ም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ከተማ የ26 ሚሊየን ዶላር የሎተሪ ዕጣ ባለዕድለኛዋ  ሴት ከልብስዋ ጋር ባጠበችው ሎተሪ የዕድሉ ተጠቃሚ ሳትሆን መቅረቷ ተዘገበ፡፡

የሎተሪ ዕጣው ባለዕድለኛ ሰው ገንዘቡን መረከብ የነበረበት የመጨረሻ ቀን ትላንት ሐሙስ የነበረ ሲሆን ቀደም ባለው ቀን ረቡዕ አንዲት ሴት ወደ ሎተሪ ሽያጭ ቢሮ በመምጣት ዕድለኛ የሚያደርጋትን ቲኬት ከልብሶች ጋር እንዳጠበቸው ለሽያጭ ሰራተኞች መግለጿ ተነግሯል፡፡

የሎተሪ ዕድለኛዋ የሎተሪ ቲኬቱን ከውስጥ ሱሪዋ ጋር በስህተት ማጠቧን መግለጿን ኢስፒሬንዛ ሄርናንዴዝ የተባለች የድርጅቱ ሰራተኛ ለኋይተር ዕለታዊ የዜና ምንጭ መናገሯን  ዘገባው አስነብቧል፡፡

ባለዕድለኛዋ ሴት ትኬቱን መግዛቷን የቪዲዮ ማስረጃዎች  በመገኘታቸው ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ካሊፎርኒያ የድርጅቱ ዋና ቢሮ መላኩም ተዘግቧል፡፡

የቀረበው ቅሬታ  ውጤታማ እንዲሆን ቅሬታ አቅራቢ ሰዎች የጠፋባቸው ቲኬት የእነሱ ስለመሆኑ የሚያመለክት የቲኬቱ የፊት ወይም የጀርባ ምስል በፎቶ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የድርጅቱ ቃል-አቀባይ የሆኑት ካቲ ጆንስተን ተናግረዋል፡፡

26 ሚሊየን ዶላር አሸናፊ የሚያደርገው የሎቶሪ ቲኬቱ ቁጥር 23, 36, 12, 31, 13, እና የማስተዛዘኛ ቁጥሩም 10 እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ባለቤት ካልቀረበ 19.7 ሚሊየን ዶላሩ በካሊፎርኒያ ከተማ ለሚገኙ የህዝብ ትምህርት ቤቶች የሚሰጥ መሆኑንም ተገልጿል፡፡

በሀገራችንም በርካታ ሰዎች የሎቶሪ ቲኬት በመግዛት የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እንደሚደርጉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የሎተሪ ቲኬት የሚገዙ ሰዎች መሰል አሳዛኝ ገጠመኝ እንዳይከሰት በሎተሪ ቲኬት አያያዝ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ይሆናል፡፡ መረጃው የኤቢሲ ኒውስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም