በአልጄሪያ በአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ለተሳተፈው ልዑክ የምስጋናና የሽልማት ስነ ስርአት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በአልጄሪያ በአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ለተሳተፈው ልዑክ የምስጋናና የሽልማት ስነ ስርአት ተካሄደ
አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 በአልጄሪያ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ተሳትፎ ላደረጉና ሜዳሊያ ላመጡ ስፖርተኞች የምስጋናና የሽልማት ስነ ስርአት ትናንት ማምሻውን በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል። የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ከሐምሌ 11 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ በ11 ወርቅ፣ ስምንት የብርና ስድስት የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 25 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሰባተኛን ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ የ20 ሺህ፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡ የ15 ሺህና የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡ የ10 ሺህ ብር ሽልማት የተበረከተ ሲሆን በብስክሌት ውድድር ሶስት የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው በልዩ ተሸላሚነት የ50 ሺህ ብር ተበርክቶላታል። የውድድሩ ሆነው ሜዳሊያ ያላመጡ ስፖርተኞችና የህክምናና የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ የልዑካን ቡድኑ አባላት እያንዳንዳቸው የአምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። አሰልጣኞች በስራቸው የሚገኙ ተወዳዳሪዎችን ይዘው ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ከ20 እስከ 40 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል። በአልጄሪያው ውድድር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ በቀለ ቡድኑ ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ልዩ ተሸላሚ በሚል የ30 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል። በአጠቃላይ ለልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ አሎምፒክ ኮሚቴ ለልዑካን ቡድኑ ከ820 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል። በስድስት የስፖርት ዓይነቶች የተካፈለችው ኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌትና ቦክስ ሜዳሊያ አግኝታለች። በጠሬጴዛ ቴኒስና በካራቴ ስፖርቶች ብትሳተፍም ሜዳሊያ አላመጣችም። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ በቀለ በስፖርተኞች፣ በአሰልጣኞችና ሌሎች አመራሮች መካከል የነበረው መከባበርና መደማመጥ እንዲሁም ስህተት ሲሰራ ሃላፊነት የመውሰድ ጉዳይ በጣም ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል። ስፖርተኞቹ የነበራቸው አንድነትና የቡድን መንፈስ በውድድሩ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች አልፈው ውጤታማ በመሆን የአገራቸውን ስም ማስጠራት እንዲችሉ ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል። በአልጄሪያ የታየው አጠቃላይ የቡድን መንፈስ ኢትዮጵያ በሌሎች ውድድሮች ላይ ስትሳፍ መቀጠል ያለበት መልካም ልምድ እንደሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵያ በውድድሩ እምብዛም በማትታወቅባቸው ስፖርቶች የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣቷ ለሌሎች ስፖርቶች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያ ውጤት አታመጣባቸውም በተባሉ የስፖርት ዓይነቶች ውጤት እንደመጣና በብስክሌት የተገኘው አራት የወርቅ ሜዳሊያና በቦክስ የተገኘው ወርቅ ሜዳሊያ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል እንደሆነ ገልጸዋል። የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ ለሌሎች ስፖርቶች ትኩረት ሰጥታ ብትሰራ ውጤታማ እንደምትሆን ያሳየ በመሆኑ መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባው አመልክተዋል። በውድድሮች የተሻለ ውጤታማ ለመሆን ሰፊ ቅድመ ዝግጅትና የመንግስት ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው ዶክተር አሸብር ያስረዱት። መንግስት በአጠቃላይ ለልዑካን ቡድኑ ዝግጅትና የአልጄሪያ ቆይታ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገም ጠቁመዋል። በአጠቃላይ በውድድሩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ ስፖርተኞች ምስጋና አቅርበዋል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው የተገኘው ውጤት ትልቅ ነው በቀጣይ ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ከዚህ በላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። የተገኘው ውጤት በአገሪቷ የስፖርት አካዳሚዎችና የክልል የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት በታዳጊዎች ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ፍሬ እያፈራ መሆኑን አመላካች እንደሆነም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። የስፖርት አካዳሚዎችን በማስፋት፣ የክልል የስልጠና ማዕከላትን አቅምን በማጎልበትና ለውድድሮች ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ሚኒስቴሩ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስረድተዋል። የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በአልጄሪያ ባደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሌሴቶ ከአራት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን አራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ እንድታዘጋጅ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ከአራት ዓመት በፊት ሁለተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በቦትስዋና ርዕሰ-መዲና ጋቦሮኒ ሲካሄድ ኢትዮጵያ 14 የወርቅ፣ ስድስት የብር እና ሰባት የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት አምስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ አይዘነጋም።