ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ 'ሐቅ' መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ እናስረዳለን - የእስልምና እምነት ተከታዮች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 05/2013(ኢዜአ) ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ግድቡ የኢትዮጵያ ሐቅና መብት መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ እንደሚያስረዱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።

ኢዜአ በ1 ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል አከባበር ላይ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉንም አንድ የሚያደርግ ነው ይላሉ።

አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን አሁን ግድቡን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ጫናዎች እየበረቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ከዚያም የሚነሱ የአገር ጠላቶችን ማሳፈር የሚቻለው ለግድቡ ግንባታ የሚደረገውን አስተዋጽኦ በማጠናከር እንደሆነም ተናግረዋል።

ወጣት አብዱራዛቅ አብደላ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ለግድቡ ግንባታ ከምናደርገው ድጋፍ ባሻገር የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ 'ሐቅ' መሆኑን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለዓለም ሕዝብ መናገር አለብን ነው ያለው።

ለግድቡ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙ ከመንግስት ጎን እንደሚቆም እምነት አለኝ የሚሉት ደግሞ ሼህ ዓሊ ሙሃመድ ናቸው።

ሙስሊሙም ይሁን ክርስቲያኑ ሁሉም ያለ ልዩነት 'ከሁሉም በላይ ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያዊያን እንጂ የማንም አለመሆኑን አውቀን የራሳችንን ሃብት የመጠቀም መብታችንን ማረጋገጥ አለብን" ብለዋል።

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ከድህነት መውጫ መንገዳቸው መሆኑን አውቀው ሊተባበሩ እንደሚገባ የሚጠይቁት ደግሞ አቶ መሀመድ ሁሴን ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን በስደት የሚሰቃዩበት ድህነት እንዲወገድ በውስጥም በውጪም ያለው ሙስሊም ሕብረተሰብ መተባበር አለበት ነው ያሉት።

ወጣት ኢብራሂም ከድር በበኩሉ የአገር ጠላት ካልሆነ በቀር ማንም በግድቡ ጉዳይ አይደራደርም ይላል።

የሕዳሴ ግድብ የአሁኑን ትውልድ የኤሌክትሪክ ፍላጎት የሚያሟላና ለመጪውም ትውልድ የሚተላለፍ ሃብት በመሆኑ ይህን ጠቃሚ የልማት ውጥን ከግብ እንዲደርስ መስራት እንደሚገባ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም