ቀጥታ፡

የአንድ አገር ምሰሶ የሆነውን አንድነት አስጠብቆ ለማስቀጠል ሕዝበ ሙስሊሙ ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 05/2013(ኢዜአ) የአንድ አገር ምሰሶ የሆነውን አንድነትን አስጠብቆ በማስቀጠል ረገድ ሕዝበ ሙስሊሙ ግንባር ቀደም መሆን እንደሚገባው ተገለፀ።

1 ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላው ኢትዮጵያ ዛሬ ተከብሯል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከማለዳው ጀምሮ በተከበረው 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል የእምነቱ ተከታዮች በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት ታድመዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ፣ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ "ግድቡ የእኔ ነው" የሚል መልዕክት በማንገብም ድምጹን ለዓለም አስተጋብቷል።

ለአንድ አገር ሠላምና አንድነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው ያሉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ ይህን አጠናክረን ወደ ልማታችን ልንጓዝ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሠላምና አንድነታቸውን በማስጠበቅ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ጠላትን ሊያንበረክኩ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሀጂ ሱልጣን አማን ኤባ 'እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሰን' በማለት ለእምነቱ ተከታዮች መልዕክት አስተላልፈዋል።

ረመዳን ከቃል ባለፈ በተግባር የታጀበ ጾም ብቻ ሳይሆን የመተሳሰብ፣ የፍቅር የመረዳዳትና የአንድነት ወር መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው የረመዳን ወር የነበረው መነቃቃትና መተሳሰብ የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

አንድነት የአገር ምሰሶ በመሆኑ ይህን አስጠብቆ በማስቀጠል ረገድ ሕዝበ ሙስሊሙ ግንባር ቀደም መሆን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳንን ወር በፆምና ፀሎት፣ በይቅርታ፣ በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ አርዓያነት ያለው ተግባር በመፈፀም ማሳለፉን የገለጹት ደግሞ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው።

ይህ ረመዳንን ብቻ ጠብቀን የምናደርገው ሳይሆን ሁል ጊዜ መቀጠል ያለበት መልካምነት ነው ብለዋል።

የዘንድሮ ረመዳን ወር በተለይም በአዲስ አበባ ከሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች ጋር በመሆን አንድነትን በሚያሳይና የአብሮነት እሴቶች ላይ ያንዣበበውን አደጋ በሚቀለብስ መልኩ መካሄዱንም አውስተዋል።

አገሪቱን ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚታትሩ ሀይሎች በብሄርና በሃይማኖት ስም ኢትዮጵያዊያንን ለመነጣጠል ስውር ዓላማቸውን በራሳችን እጅ ለማሳካት የሚያደርጉት ሙከራ እንደማይሳካ መታየቱንም አንስተዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ኢትዮጵያዊያን ታላቁ የህዳሴ ግድብን ከፍፃሜ ለማድረስ በአንድ ልብና ጽናት የሚቆሙ መሆኑን 'ለመላው ዓለም ማረጋገጥ እንወዳለን' ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ፈጣሪ የሰጣትን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም መብቷ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ብለዋል።

በግድቡ ዙሪያ ከየትኛውም የውጭ ሀይል የሚመጣን ኢ-ፍትሀዊ ጫና የማንቀበለው ከአገራዊ ስሜት በላይ ማንም ሳይበደል ለእውነትና ለአገራዊ ጥቅም መቆም ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን ሰለምንረዳ ነው ብለዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግራትን መጪውን ምርጫ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ለማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙ የማይተካ ሚና እንዲጫወት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም