በሀገሪቱ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ሁሉ በጋራ እንቆማለን- ኡስታዝ መሐመድ አሚን - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ሁሉ በጋራ እንቆማለን- ኡስታዝ መሐመድ አሚን
ጅማ/መቱ፤ ግንቦት 05/2013 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙን በማስተባበር በሀገሪቱ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች በጋራ በመቆም አብረን እንሰራለን ሲሉ የጅማ ከተማ አስተዳደር የእስልምና ጉዳይ ፕሬዚደንት ኡስታዝ መሐመድ አሚን ተማም ገለጹ።
1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በጅማና መቱ ከተሞች በድምቀት ተከበረ።
በጅማ ከተማ በተከበረው የኢድ በዓል ላይ ኡስታዝ መሐመድ አሚን ተማም ባደረጉት ንግግር በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደጀመር ነው ለመጨረስ መስራት ይገባናል ብለዋል።
ያልተገባ አስተሳሰብን በማስወገድ ሰርተን ሀገራችንን ለመለወጥ መትጋት አለብን፤ ህዝበ ሙስሊሙን በማስተባበር በሀገሪቱ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ሁሉ በጋራ እንቆማለን አብረን እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ኢሊያስ ሸረፉ ባስተላለፉት መልዕክት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ አንድነትና የብልጽግና እንዲሆን በመመኘት ያለው ለሌለው በማካፈልና ከኮሮና በመጠበቅ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የከተማውንና የአካባውን ሰላም በመጠበቅና የልማት ስራችንን በማከናወን ለቀጣዩ ምርጫ በመዘጋጀት ሀገራችንን ወደ ተሻለ እድገት ለማሻገር ሁላችንም መስራት አለብንም ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በዓሉ በመቱ ከተማ ስታዲየም በጋራ የሰላት ስነስርዓት በተከበረበት ወቅት የኢሉባቦር ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ጣሂር ከሊል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዓሉን በመተሳሰብና ያለው ለሌለው በማካፈል አብሮነታችንን ማሳየት መልካምና አላህ የሚፈለገው ነው፤ በዓሉን በጋራ ስናከብርም የኮሮናን ቫይረስ መከላከያ መመሪያዎችም ሳንዘናጋ መተግበር አለብን ብለዋል።
በስነስርዓቱ ከተገኙት የመቱ ነዋሪዎች መካከል አቶ ያሲን ነገሰ በሰጡት አስተያየት፤ የኢድ ሰላቱን በጋራ ካደረግን በኋላ ወደየቤታቸን ስንመለስ ያለንን በጋራ ሆነን በመተሳሰብና ለሌላቸው በማካፈል ማሳለፍ የእምነታችን መርህ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መከላከያ መመሪያዎች መተግበር እንዳለበትም አመልክተዋል።
አቶ አብዲ ሐሰን በበኩላቸው፤ዕለቱ ሁሉም በደስታ እንዲያሳልፍ በመተሳሰብ መሆን አለበት ብለዋል።
የኢድ ወር ከአላህ ጋር ይቅርታን በመለመንና ፍቅርንና በማሳየት የምንቆይበት የተባረከ ወር ነው፤
በጾም ወቅት ስናደርግ የነበርነውን መልካም ተግባር ማስቀጠል ይጠበቅብናል ያሉት ደግሞ ሼህ አንዋር ተማም ናቸው።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ መገርሳ ማሞ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ ካሉ በኋላ በዓሉን ስናከብር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጥንቃቄ መመሪያዎች ባለመዘናጋት መሆን አለበት ብለዋል።