ቀጥታ፡

ምርጫው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ሀዋሳ፤ ግንቦት 4/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በምርጫው ዙሪያ ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤  መንግስት ሰላምን ከማስከበሩ በተጓዳኝ ምርጫው የህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል።

የመራጮች ምዝገባ፣ የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳና ሌሎች የቅድመ ምርጫ ተግባራት  በሰላማዊ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ  ከሚንቀሳቀሱ  ተፎካካሪ  ፓርቲዎች ጋር በትብብር  እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ከባድ ቀውስ ገጥሞ  እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደስታ፤ ከህዝቡ ጋር በመተባበር በተከናወነው ስራ  ወደ ቀደመ ሰላም መመለስ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

በምርጫው ሂደት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ሰላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ተከታትሎ ለሚመለከተው አካል መጠቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምርጫው ሰላማዊና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ መላው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ያስፈራቸው አንዳንድ ሃገራትና ግለሰቦች በእጅ አዙር እያካሄዱ ያሉትን ሴራ መመከትና ለብሄራዊ ጥቅማችን በአንድነት መሰለፍ ይጠበቃል ብለዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ካንቲባ ረዳት ፕፌሰር ጸጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውን  በማጠናከር  ለከተማዋ  ሰላምና ጸጥታ ሊረባረቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉና ምርጫው ካለምንም  የጸጥታ  ችግር  በሰላም  እንዲያበቃ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው ነዋሪው እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት  እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አዛለች ጋቢሶ በሰጡት አስተያየት፤  ህዝቡ  ነቅቶ ሰላሙን እየጠበቀ እንደሚገኝ አመልክተው  ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የሲዳማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አቢኖ ማሴቦ በበኩላቸው፤  ዘላቂ ሰላም  የሚረጋገጠው እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ከራሱ ጀምሮ የሚጠበቅበትን ሲወጣ  መሆኑን ገልጸዋል።

በግላቸው ከቤት ተከራዮቻቸው ጋር በመምከር የተለየ ነገር ሲኖር በትኩረት እንደሚከታተሉና ይህን ሁሉም በየአካባቢው ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሰላምን በማጠናከር በልማት የበለጸገች ሀገር ለመገንባት መስራት ከዜጎች  የሚጠበቅ  ሃላፊነት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ጸሀይ ደቦጭ ናቸው።

በምርጫው ሽፋን ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ቢያጋጥማቸው  ለጸጥታ ሃይሉ አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም