በእስልምና ቀን መቁጠሪያ ዓመተ ሒጅራ እና ጨረቃ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 04 / 2013 (ኢዜአ) "በጨረቃ ቀመር የሚሰላው የእስልምና ቀን መቁጠሪያ 'ዓመተ ሒጅራ' ጥልቅ ሳይንሳዊ ምርምር ነው" ሲሉ ሼኽ መሃመድ የሱፍ ገለጹ።

በስነ ፈለክ ሳይንስ ከስርዓተ ፀሐይ ፈለኮች አምስተኛዋ ግዙፍ ፈለክ ጨረቃ እንደሆነች ይጠቀሳል።

ይህቺ የሕብረ ከዋክብቷ ግዙፍ ፈለክ ጨረቃ እንቅስቃሴዋ ከዘመን አቆጣጠር ጋር ጥብቅ ሳይንሳዊ ዝምድናም አለው።

በስነ ፈለክ ሳይንስ የወቅቶች መፈራረቅ ፀሐይ፣ መሬትና ጨረቃ በራሳቸው ምህዋር የሚያደርጉትን ሽክርክሪት ተከትሎ እንደሚከሰት ይገለጻል።

በእስልምና ሃይማኖት ዘንድ ደግሞ ጨረቃ 'ቀመሪያ' ለተሰኘው የዘመን አቆጣጠር መሰረት ስትሆን፣ በእስልምና እምነት ተከታይ አገሮችም በመልከ ብዙ አገራዊ ትዕምርትነት ትወሰዳለች።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ሼኽ መሃመድ የሱፍ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ እስልምና ጥልቅ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ዕውቀቶች እንዳሉት አብራርተዋል።

ከእነዚህ መካከል ከሳይንሱ ጋር የሚመሳሰለው የጨረቃ የዓመተ ሂጂራ ዘመን አቆጣጠር ሲሆን በእስልምና ዘመን የሚሰላው 'ሸምስያ' በሚሰኘው የፀሐይ አቆጣጠር ሳይሆን 'ቀመሪያ' በሚሰኘው የጨረቃ ስሌት ስለመሆኑ ያነሳሉ።

በዚህ እስልምና በሚከተለው ስሌትም 12ቱ ወራትና ወርኅ ጳጉሜን ጨምሮ በከዋክብት የሚሰላበት ጥልቅና ውስብስብ ሳይንሳዊ ዕውቀት ስለመኖሩ አንስተዋል።

በዓረብኛው 'መናዚል' የሚሰኙ 28 ከዋክብት ስለመኖራቸው የሚያነሱት ሼኽ መሃመድ፤ ፀሐይና ጨረቃን ጨምሮ ሁሉም ከዋክብት የራሳቸው ስራ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የቀንና የሌሊት ርዝመት ልዩነትም ምክንያት እንዳለው በዚህ ዕውቀት ውስጥ ስለመኖሩ አንስተዋል።

እንደ ሼኽ መሃመድ ገለጻ፤ ከረመዳን ጾም በኋላ ነገ የሚከበረው 1 ሺህ 442ኛው ኢድ አልፈጥር በ29 እና በ30 ቀናት ልዩነት የሚከሰተው በአጋጣሚ ሳይሆን ሰፊ የሳይንስ ምርምር ባለው በቀመሪያ ስሌት መሰረት ነው።

በዚህ በእስልምናው የቀመሪያ የዘመን አቆጣጠር ዕውቀትም መምህሩ ለደቀ መዛሙርቱ በተግባርና በንድፈ ሃሳብ የሚያስተምርበት ስርዓት እንዳለ ይገልጻሉ።

ይህም በቅዱስ ቁርዓን ስለመቀመጡ አስታውሰው፤ የሒጅርያ አጀማመርም ነብዩ መሃመድ ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ጉዞ መነሻ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም