ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኞችና የበረኛ አሰልጣኝ መረጠ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 26/2010 ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኞችና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ታውቀዋል። ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው የተመረጡት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የምክትል አሰልጣኞችና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ዝርዝር አሳውቀዋል። በዚሁ መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝና የሃዋሳ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ቡና የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ የብሔራዊ ቡድኑ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆነዋል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታዎችና የቅጥር ውል በመፈጸም ወደ ስራ እንደሚገቡ ተገልጿል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትናንት ባደረገው ስብሰባ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን መሰየሙን አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ ዘጠኝ ቋሚ ኮሚቴዎች አሉት። በዚሁ መሰረት የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ ኢብራሂም መሐመድ የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢና አቶ አብዱራዛቅ ሐሰን የአንደኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነዋል። ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን የሴቶች እግር ኳስ ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ የዳኞች እና ታዛቢዎች ኮሚቴ፣ የማርኬቲንግ ኮሚቴ ሰብሰቢ አቶ አበበ ገላጋይ፣ የፀጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሊሚራህ መሐመድና የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በመሆን ተሰይመዋል። የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት ሰዎች ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት ሆነው የተመረጡ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም