ቀጥታ፡

ሰብልን ከወፎች ጥቃት የሚከላከል የ"ድሮን" ቴክኖሎጂ ትውውቅ ተካሄደ

ሀዋሳ ፣ ግንቦት 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) "ቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ" የተባለው ድርጅት በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውንና ሰብልን ከወፎች ጥቃት የሚከላከል ሰው ሰራሽ በራሪ (ድሮን) ቴክኖሎጂ አስተዋወቀ።

ድርጅቱ ሰብልን ከወፎች በመከላከል ተግባር የሰለጠኑ አራት ጭልፊት "ፋልከን" ወፎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ዝዋይ በሚገኘው የወይን እርሻው ላይ አሰማርቷል።

ድሮን ቴክኖሎጂን ለግብርና ዘርፍ ለማስተዋወቅ በባቱ ከተማ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ የወይን እርሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይትባረክ ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በ247 ሄክታር መሬት ላይ ከሚያካሂደው የወይን ልማት ውስጥ 202 ሄክታሩ ምርት ይሰጣል።

በልማቱ ለነጭ እና ቀይ ወይን ጠመቃ የሚያገለግሉ 10 ዓይነት ዝርያዎች እየለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

"በወይን እርሻው ላይ በወፎች የሚደርሰውን ጥቃት ጅራፍ በማጮህና በሌሎችም ባህላዊ ዘዴዎች ለመከላከል ጥረት ቢደረግም ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም" ብለዋል።

ወፎቹ የደረሰን የወይን ዘለላ ሲመገቡ ፈንገስ በመፍጠር የወይኑን ምርትና ጥራት በማበላሸት በወይን ጠመቃ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደረቃማ አየር ምክንያት ከኬንያና ታንዛኒያ ጭምር ወደ አገር ውስጥ በመፍለስ በርካታ የወፍ ግሪሳዎች በወይን እርሻው ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረሳቸውን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን ላይ 25 በመቶ የምርት መቀነስ ችግር በወፎች ጥቃት ማጋጠሙን አውስተዋል።

ድርጅቱ ይህንን ችግር በመረዳት በዓለም ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የወፎች መከላከያ ጥበቦችን ለኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ ድርጅቱ ወይን እርሻው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሠለጠኑ አራት የወፍ ዘሮችንና ለዚሁ ተግባር ተብሎ የተሠራ እርሻን ከወፎች ጥቃት የሚከላከል ዘመናዊ ሰው ሰራሽ ወፍ መሰል በራሪ ድሮን ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን አመላክተዋል።

"በዚህ ዘዴ ለጥቃት የመጡ ወፎችን ለብዙ ሰዓት በማጫወት ሰማይ ላይ እንዲቆዩ በማድረግ የወይን ምርቱን ከጥቃት በመከላከል ጥራት ያለው ምርት መሰብሰብ ችለናል" ብለዋል።

ከውጭ የገቡት ወፎችና ድሮን በአገሪቱ አዕዋፍ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማያስከትሉ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት መረጋገጡን ገልጸዋል።

የቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ማናጀር አቶ ገብረስላሴ ስፍር በበኩላቸው፤ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው የግብርና ቦታዎች ወፎችን ለማግለል ሰው ሰራሽ በራሪ ወፎች መጠቀም ምን ያህል ውጤታማና ጉዳት አልባ መሆኑ እንደተጠና ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ወይኑ ምንም ሳይነካካ ወደ ምርት እንዲደርስ ስለሚያደርገው የጥራትና ጣዕም መሻሻል እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂውን በሀገር ውስጥ ለማስፋፋት ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በቅርበት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም