ቀጥታ፡

የሰላም ሚኒስቴር ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ በጋራ ለመስራት ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል ጸጥታ ተቋማት ጋር ተፈራረመ

ግንቦት 4/2013 (ኢዜአ) የሰላም ሚኒስቴር 6ተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል ጸጥታ ተቋማት ጋር ተፈራረመ።

የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ስነ-ስርዓቱ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

ስምምነቱን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ከየተቋማቱ ተወካዮች ጋር አድርገዋል።

ስምምነቱ የተደረገው ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽንና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ነው።

የስምምነቱ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው በለያቸው አካባቢዎች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ለማድረግ ነው።

በዚህም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና የአካባቢውን የጸጥታ ሁኔታ የሚያውቁ ሚሊሻዎችን በማሰልጠን ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ስራ እንደሚሰራ ነው የተገለጸው።

የመግባቢያ ስምምነቱ በቀጣይ ከለየሎች ክልሎች ጋር የሚደረግ ሲሆን በዛሬው ስምምነት ከተጠቀሱት ክልሎች የተውጣጡ ሁለት ሺህ የሚሊሻ አባላት የስነ ልቦና ዝግጁነት ስልጠና ወስደው ስምሪት የሚሰጣቸው ይሆናል ተብሏል።

የሚመለመሉ የሚሊሻ አባላት የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ የሚያውቁ፣ በመልካም ስነ-ምግባራቸው ተቀባይነት ያላቸውና በሌሎችም መስፈርቶች እንደሚመረጡ ተገልጿል።

እነዚህ የሚሊሻ አባላት እስከ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የስነ-ልቦና ዝግጁነት ስልጠናቸውን ጨርሰው በተመረጡ ቦታዎች ላይ የሚሰማሩ ይሆናል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አሸባሪ ብሎ የሰየማቸው ቡድኖች የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በስምሪቱ ትኩረት እንደሚደረግባቸውም ነው የተመለከተው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የጸጥታ ኃይሉ እያከናወነ ባለው የተቀናጀ ተግባር እስካሁን ያለው የምርጫ ሂደት ሰላማዊ መሆኑን ገልጸዋል።

"በቀጣይም ዛሬ በተደረገው ስምምነት መሰረት የሚሊሻ አባላትን አቅም በማጠናቀር በምርጫ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ይሰራል" ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴር ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም