በዜጐች መካከል ፍቅርና አንድነትን የሚያጐለብቱ ተግባራትን አጠናክረን ማስቀጠል አለብን - የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
በዜጐች መካከል ፍቅርና አንድነትን የሚያጐለብቱ ተግባራትን አጠናክረን ማስቀጠል አለብን - የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮች
ፍቼ፣ ግንቦት 4/2013/ኢዜአ/ በዜጐች መካከል ፍቅርና አንድነትን የሚያጐለብቱ ተግባራትን አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል ሲሉ በፍቼ ከተማ የሚገኙ የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ገለጹ።
በከተማው አስተዳደርና በነዋሪዎች ትብብር የረመዳን ጾምና የኢድ አል ፈጥር በዓልን በማስመልከት የአፍጥርና አቅመ ደካሞችን የመርዳት ስነ ስርዓት ትናንት ማታ በፍቼ ከተማ ተካሄዷል።
በአፍጥር ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ የእስልምናና ክርስትና ሀይማኖት መሪዎች ስለአንድነት፣ ፍቅርና ሰላም የሚሰብኩ መልእክቶችን አስተላልፈዋል።
የሀይማኖት መሪዎቹ ባስተላለፉት መልእክት "በዜጐች መካከል ፍቅርና አንድነትን የሚያጐለብቱ ተግባራትን አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል" ብለዋል።
የፍቼ ከተማ እስልምና ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ኡስታዝ መሐመድ አወል እንደገለፁት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶችን በመጠበቅ ለሀገር ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተው ተከታዮቻቸውን እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያዊ የሆኑ የመተጋገዝ፣ የመወያየትና ይቅርታ የመባባል በጐ ተግባሮች ከፆም ወቅት ውጪም ተጠናክረው እንዲጐለብቱ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
የከተማው ነዋሪዎችና የተለያዩ ሀይማኖት ተከታዮች በአፍጥር ስነ-ስርዓት ዝግጅቱ ላይ ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ መካነ እየሱስ ቤተ-ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ዞን ተጠሪ ፓስተር ሰለሞን አየለ በበኩላቸው የቆዩ ባህላዊ እሴቶች እንዲጐለብቱ አንድነት፣ መተጋገዝና መቻቻል እንዲፀና በአፍጥር ስነ-ስርዓቱ ላይ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለወደፊቱም እሴቶቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።
የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ አቶ እስማኤል ቃሲም "የከተማው ህብረተሰብ ለሙስሊም ወገኑ ያለውን ፍቅር በአፍጥር ሥነ-ሥርዓት መግለፁ የቆየውን የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህል የሚያጐለብት ነው" ብለዋል፡፡
የአፍጥር ስነ ስርአቱ በህብረተሰቡ መካከልና መንግስት ለሕዝብ ያለውን የመተሳሰብና የመቻቻል የቆየ ባህል የሚያስታውስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአፍጥር ሥነ-ሥርዓቱ የከተማው አስተዳደር ከነዋሪዎች ጋር ሆኖ ያዘጋጀው መሆኑን የገለፁት የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ክፍሉ ከበደ ከሁለት መቶ በላይ ችግረኛ ወገኖችን ለመርዳት ከ10 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የአፍጥር ስነ ስርአቱ ሕብረተሰቡ በጎ እሴቶች ለዜጐች ሰላም ያላቸውን ትርጉም በመረዳት እንዲቻቻልና እንዲተጋገዝ ምሳሌ እንዲሆን መዘጋጀቱን ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።