ተስፋ ያልቆረጡ ጠላቶቻችን የሐይማኖት ግጭትና ጦርነት ለማስነሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይጭሩት እሳት የለም - የሲቪክ ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
ተስፋ ያልቆረጡ ጠላቶቻችን የሐይማኖት ግጭትና ጦርነት ለማስነሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይጭሩት እሳት የለም - የሲቪክ ማህበራት
ግንቦት 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) “ተስፋ ያልቆረጡ ጠላቶቻችን የሐይማኖት ግጭትና ጦርነት ለማስነሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይጭሩት እሳት የለም” ሲሉ ሶስት የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ አስታወቁ።
አገራዊ፣ ህዝባዊ እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በማስመልከት ኢትዮጵያ ትቀጥላለች፣ ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ እና ኦሞ ኢትዮጵያ አንድነትና ፍትህ ማዕከል የተባሉት የሲቪክ ማህበራት የጋራ አቋም በመያዝ መግለጫ አውጥተዋል።
ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝ ያስታወሰው መግለጫው፤ በለውጡ ያልተደሰቱ የውጭና የውስጥ ሃይሎች ግንባር ፈጥረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎልና አገራዊ ምርጫውን ለማደናቀፍ አሉታዊ እርምጃ ሲወስዱ መቆየታቸውን ገልጿል።
በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውድድር ተሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ በመቆም ባንዳነታቸውን በገሃድ ማስመስከራቸውን መገንዘቡንም አመልክቷል።
በጸረ-ኢትዮጵያዊነት የቆሙ ሃይሎች ብሔረሰቦችን ከብሔረሰቦች ለማጋጨት መሞከራቸውንና ግድያ መፈጸማቸውን ያወሳው መግለጫው፤ ሴራቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ የተገነዘበው በመሆኑ ተልዕኮአቸው መክሸፉን ገልጿል።
“በዚህ ተስፋ ያልቆረጡ ጠላቶቻችን የሐይማኖት ግጭትና ጦርነት ለማስነሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይጭሩት እሳት የለም” ሲል አስገንዝቧል።
በህዝቡ ዘንድ ለጸብ ቀርቶ ለንግግር የማይበቁ ምክንያቶችን በማጋነንና በማራገብ እልቂትን የሚናፍቁ ሃይሎች ሰሞኑን ለሁለት ታላላቅ የሃይማኖት ድርጅቶች ተቆርቋሪ በመምሰል ድብቅ የሴራ ወጥመዳቸውን እንደዘረጉ ገልጿል።
የሲቪክ ማህበራቱ በያዙት ሰባት የጋራ አቋም በህዝብና በሀይማኖት መካከል ግጭት እንዲነሳ የሚቆሰቁሱ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
የህዳሴ ግድቡን ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ወጥመድ ህዝቡ እንዳይጠለፍ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ከዚህ ቀደም ለማንኛውም ሃይማኖትና ብሔር ክብር የሌላቸው ሃይሎች የበደሉትንና የገደሉትን ህዝብ እንወድሃለን በማለት በሚያፈሱት የአዞ እንባ ህዝቡ እንዳይታለል መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የሽግግር ባለአደራ መንግስት በማለት ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንቅፋት ለመሆን የሚፈልጉ የስልጣን ጥመኞችን እናወግዛለን” ብለዋል በአቋም መግለጫቸው።
ህዝቡ የጠላት መሳሪያ ሳይሆን በሰላም፣ በእርጋታ፣ ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ ስህተቶች እንዲታረሙ በማድረግ አገሩን እንዲጠብቅ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ የህዳሴ ግድቡ እና አገራዊ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅና የለውጥ ጉዞው እንዲፋጠን በማድረግ የጠላቶቹን ቅስም በመስበት ታሪካዊ ጽናቱን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ለዘመናት የኖረውን የመቻቻልና የመከባበር ጥበባቸውን በመጠቀም ተፈጠረ የተባለውን ስህተት በማረም አገራቸውን ከውድቀት፤ ህዝባቸውንከጥፋት የማዳን ታሪካዊና ብሔራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።