ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ የምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት በዓለማዊ ክንዋኔዎች እንዳይበረዙ መጠበቅ ያስፈልጋል

ግንቦት 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ የምታከብራቸው በዓላት በዓለማዊ ክንዋኔዎች እንዳይበረዙ መጠበቅ እንደሚገባ ተጠቆመ።የበዓላቱን አከባበር ዝግጅት የሚያስተባብር ቋሚ አደረጃጀት ሊኖር ይገባልም ተብሏል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት የሰበካ ጉባዔ መምሪያ "የአደባባይ በዓላት ስኬቶችና ተግዳሮቶች" በሚል ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ትናንት ተካሄዷል።

የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ መምህር ማለዳ ዘሪሁን ቤተክርስቲያኗ የምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት ሃይማኖታዊ አስተምህሮና ስርዓትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአደባባይ በዓላቱ የቤተክርስቲያኗ ታሪክ፣ እሴትና ሀብት የሚታዩባቸው እንደሆኑም ተናግረዋል።በተጨማሪም ፍቅርና አንድነት ማስፈኛ፣ ለቤተክርስቲያን ስርዓት መገዛት ማሳያ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ተደራሽ ማድረጊያ እንዲሁም በረከት የሚገኝባቸው መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት።

የአደባባይ በዓላቱ "በአገር ውስጥ ከመከበር አልፈው ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘታቸው የዓለምን ማህበረሰብ ትኩረት እየሳቡ ይገኛሉ" ብለዋል መምህር ማለዳ።ይሁንና በቤተክርስቲያኗ የአደባባይ በዓላት ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ ያፈነገጡ ዓለማዊ ተግባራት እየታዩ መምጣታቸው በዓላቱ ተግዳሮት እንዲያጋጥማቸውና መንፈሳዊ ይዘታቸው እንዲበረዝ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ሃይማኖታዊ ክንውኖቹ ጎልተው እንዲታዩ ማድረግና በዓሉን መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ ማክበር እንደሚገባም ተናግረዋል።መምህር ማለዳ እንዳሉት፤ ምዕመናን የቤተክርስቲያኗን የበዓል አከባበር ስርዓትና መመሪያን መከታተልና ባህላዊ ክንዋኔዎችን ስርዓትን በጠበቀ መልኩ መከወን ይገባቸዋል።ባህላዊ ክንዋኔዎች ክርስቲያናዊ ትርጉም እንዲኖራቸው፤ ይሄ ካልተቻለም የባህሉን አውድ መውሰድ እንደሚቻል ነው የገለጹት።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት እንደሚገባቸውም አክለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአደባባይ በዓላት በሚከበሩባቸው ስፍራዎች የሚፈጸሙ ዓለማዊ ተግባራት ሃይማኖታዊ ስርዓቱን የሚያበላሹ በመሆናቸው ሊታረሙ እንደሚገባ ነው ያነሱት።በተጨማሪም የበዓላቱን አከባበር ዝግጅት የሚያስተባብር ቋሚ አደረጃጀት መኖር እንዳለበትና የአደረጃጀቱ መዋቅር ምዕመኑን ከቤተክርስቲያኗ ጋር የሚያስተሳስር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።ለወጣቱ ትውልድ የበዓላቱን ስርዓቶች በሚገባ ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነም አመልክተዋል።በተለይም በዓላቱ ሲከበሩ የሚኖረው ንግድና ልመና አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ተጠቁሟል።

በዓላቱን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቆጣጠርና ለመፍታት ራሱን ራሱን የቻለ መዋቅር ተሰጥቶት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አገረ ስብከት ድረስ በኮሚቴ ቢመራ ተግዳሮቶች እንደማያጋጥሙ ተገልጾ፤ ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አገረ ስብከት ድረስ በተደራጀ መንገድ እንዲተገበር ተጠይቋል።የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ተክሌ በበኩላቸው "ወጣቱን መጠቀም፣ ማስተማርና ማስተባበር ያስፈልጋል" ብለዋል።

ስነ ምግባር ያለው ወጣት እንዲፈጠር መስራት የሚቻልበትን መንገድ መመልከት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ወደ ህብረተሰቡ ለመውረድ የሚያስችሉ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የአደባባይ በዓላቱ ሃይማኖታዊ ይዘታቸው ሳይሸራረፍ እንዲከበር ምዕመኑን የማስተማርና ለማስገንዘብ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

"የአደባባይ በዓላትን ጠብቆና አስጠብቆ የሚሰጡትን ዘርፈ ብዙ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥቅም ለማስቀጠል ይሰራል" ብለዋል።የአደባባይ በዓላት የሚከበርባቸው ቦታዎች ተገቢው ክብርና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም