ቀጥታ፡

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊና ተአማኒ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

ሀዋሳ ፤ግንቦት 04/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚካሄዱ አፍራሽ ሴራዎችን በማምከን ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊ ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሀገራዊ ምርጫ ላይ ያተኮረ የፓንል ውይይት ተካሂዷል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ፍስሀ ይታገሱ በበይነ-መረብ አማካኝነት ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ጠንካራና ዴሞክራሲያዊ ሀገር መገንባት የሚቻለው ነፃ፣ ፍትሀዊና ተአማኒ ምርጫ ማካሂድ ሲቻል ነው ብለዋል።  

ኃያላን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በምርጫ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አዝማሚያ እንዳለው ገልጸዋል።

ለዚህም ማሳያው ከሰሞኑ አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ ሂደት ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም ማለታቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ይህም ኃያላን ሀገራት ምርጫውን እንደ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው ጫና በመፍጠር ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድቡ ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም ለማስቀየር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ መሆኑን አቶ ፍስሀ ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥም ግጭቶቻና መፈናቀሎች በማብዛት ምርጫውን የማጠልሸትና ቅቡልነት ያለው መንግስት እንዳይመሰረት የማድረግ ዓላማ ያነገበ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ተባባሪ ኃይሎች በምርጫው ሽፋን ኢትዮጵን ለማዳከም የሚያካሄዱትን አፍራሽ ሴራዎችን በማምከን የምርጫው ሂደት ፍፁም ሠላማዊ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ የማራመድ ተስፋን ይዞ የመጣ ቢሆንም  ሥጋቶችም እንዳሉ ተናግረዋል።

ግብፅና አጋሮቿ ኢትዮጵያን በማተራመስ የህዳሴውን ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል።

ሁላችንም የምናሸንፍበትን ምርጫ ማካሄድ የምንችለው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ለዚህም ሂደቱን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በማድረግ ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግስት ለመገንባት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ በተለይ በግብፅ አቀነባባሪነት ከፍተኛ የሆነ የሥነ-ልቦናና የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ተከፍቶባታል ያሉት ደግሞ በአሜሪካ የአሪዞና ግሎባል ኒዩሮ ሳይንስ ሜንታል ሄልዝ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዮናስ ገዳ ናቸው።

በጎረቤት ሀገራት አማካይነትም ወታደራዊ ትንኮሳ እየተፈፀመባት መሆኑንና ይህንን ለመመከት ደግሞ ኢትዮጵዊያን ቅድሚያ ለሀገር በመስጠት መንቀሳቀሰ እንደሚኖርባት አመልክተዋል።

ፖለቲከኞች ፅንፍ የያዙ አቋሞቻቸውን ወደ መሀል ለማምጣትና በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ተቀራርበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ምርጫ ዙሪያ በመንግስት በኩል የተከናወኑ ሥራዎች ካለፉት ዓመታት የተሻሉ ቢሆንም በውጭና በውስጥ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሥጋት መደቀኑን ተናግረዋል።

ይህንን በመገንዘብ  የምርጫው ሂደት  ሠላማዊ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ዩነቨርሲቲው መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ታምራት አሰፋ በሰጡት አስተያየት፤ የምናስበውን ማሳካት የምንችለው ሀገር ሠላም ስትሆን በመሆኑ እንደ አባቶቻችን ለሀገር ህልውና ቅድሚያ መስጠት ይገባናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የብሔር፣ የሐይማኖትና የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ብዝሀነት ለክፋት አጀንዳ በመጠቀም የሀገሪቱ ጠላቶች የጥፋት ሴራ እየጠነሰሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች በህግ-አግባብና ውይይት ለመፍታት የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙትን የቃል ኪዳን ሰነድ ማክበር እንደሚጠበቅባቸውና ፓርቲያቸው በዚህ ረገድ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በፓናል ውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም