በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቃዮችን የመመለስና የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቃዮችን የመመለስና የማቋቋም ስራ እየተከናወነ ነው
ግንቦት 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቃዮችን የመመለስ፣ የማቋቋምና ራሳቸውን እንዲደጉሙ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
የወረዳ ኮማንድ ፖስት አባላት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋምና ለሠብዓዊ ድጋፍ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት ከወረዳ ኮማንድ ፖስት አባላትና አመራሮች ጋር የስራ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።
ተፈናቃዮችን በመመለስ፣ በመልሶ ማቋቋምና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው ግምገማ ቀጣይ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የሠብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትና ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች መዘግየት መኖሩን የወረዳ አመራሮች አንስተዋል።
የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ተፈናቃዮችን ለመመለስ በእቅድ የተደገፈ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
"የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት መዘግየት የወረዳዎች ችግር መሆኑን ለይተናል" ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ፤ ለፌዴራል መንግስት ጥያቄ የቀረበ በመሆኑ ሳይዘገይ እንደሚፈታ አረጋግጠዋል።
የፈረሱና የተቃጠሉ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የጸጥታ ሃይል፣ የወረዳ አስተዳደሮችና ተማሪዎችን ያሳተፈ የተቀናጀ ርብርብ መካሄድ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።
የጉባ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ባኪ ደርድም ወረዳው እስካሁንም 10 ሺህ 820 ተፈናቃዮችን መመለሱን ገልጸዋል።
ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የገቡትን ጨምሮ 8 ሺህ ተፈናቃዮችን ለመመለስ የአገር ሽማግሌዎችን ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ባኪ ገለጻ፤ የተመለሱ ተፈናቃዮችን በሁለት ማዕከላት በማስገባት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቢምር አምሳዬ በበኩላቸው በአጠቃላይ ፎቶ መንጃሬና ገነተ ማርያም ላይ ከ1 ሺህ 900 በላይ ተፈናቃዮችን ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ አብርራርተዋል።
"ተፈናቃዮች ራሳቸውን እንዲደጉሙ በጊዜያዊነት መሬት በመስጠት እንዲያለሙ የማድረግና መኖሪያቸውን የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ ነው" ያሉት ደግሞ የወንበራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ አዲሱ ናቸው።