በመዲናዋ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ 45 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በዚህ ዓመት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ 45 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በዚህ ዓመት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ
ግንቦት 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመዲናዋ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 42 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በዚህ ዓመት ለምረቃ እንደሚበቁ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎችና ከከተማዋ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹን የግንባታ አፈፃፀም ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው የምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የጨፌ ሜዳ፣ የአፍንጮ በር ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የራስ ሃይሉ መዋኛ ገንዳን ተመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር በላይ ደጀን በከተማዋ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሆነባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታቸው ተጠናቆ በተያዘው ዓመት ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ብለዋል።
ዘንድሮ ከሚጠናቀቁት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል በተለያዩ ችግሮች ለብዙ ዓመታት የተጓተቱና በዚህ ዓመት የተጀመሩም ይገኙበታል።
ጉብኝቱ ከተካሄደባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል ግንባታው ለዓመታት የተጓተተውና አሁን ተጠናቆ ውሃ እየተሞላ የሚገኘው የራስ ሃይሉ መዋኛ ገንዳ አንዱ ነው።
በዚህ ዓመት ግንባታቸው ከተጀመሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደግሞ የአፍንጮ በር ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።
ሌላው በዚህ ዓመት የተጀመረው በፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚገኘው ጨፌ ሜዳ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የእግር ኳስ ሜዳን ጨምሮ ሦስት በአንድ ሜዳ አካቶ ይዟል።
የዚህ ሜዳ ግንባታ 90 በመቶ የደረሰ ሲሆን ቀሪ ስራዎችን በ15 ቀናት በማጠናቀቅ ለአግልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ በጉብኝቱ ላይ ተገልጿል።
በኮሚሽኑ የማዘውተሪያ ስፍራዎችና የስፖርት ልማት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዩ ኮሚሽኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፋራዎች ግንባታ በስፋት እያከናወነ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።
በከተማዋ የሚከናወኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ግንባታ መጓተት ችግሩን እንዳባባሰው ጠቁመዋል።
በተያዘው ዓመት ለረጅም ጊዜ የተጓተቱና አዲስ የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ስራዎች በፍጥነት እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የአመራሩን ቁርጠኝነትና ከዚህ በፊት በፕሮጀክቶች ግንባታ የነበሩ ክፍተቶች ታውቀው የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ መደረጉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ ወጣቶችም በከተማዋ የማዘውተሪያ ቦታዎች ግንባታ ከነበረበት ሁኔታ መሻሻል እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎቹ ከእግር ኳስ ሜዳ በተጨማሪ ሌሎች የስፖርት አይነቶችን እንዲያካትቱ በሚያደርግ መልኩ እየተገነቡ ስለመሆናቸው ማየታቸውንም ገልጸዋል።
ይህም በርካታ ወጣቶችን በአልባሌ ቦታ ከመዋል የሚታደጋቸው ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ስፖርተኞች እንዲፈሩ ያደርጋል ብለዋል።
ይሁንና አሁንም በመዲናዋ ካለው ወጣት አንጻር ተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት።