ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ተደርሷል - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ተደርሷል - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
ግንቦት 4/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር እንደሚሰራ አስታወቀ።
በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች በኔዘርላንድስ የማጣሪያ ውድድር እንደሚያካሂዱም ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በፌዴሬሽኑ መካከል 'የህግ ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለሚካፈሉ አትሌቶች ተገቢው እንክካቤና ወጪ እየተሸፈነ አይደለም በሚል አለመግባባት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና በቅርቡ ከኦሊምፒክ ኮሚቴው ጋር የጋራ ውይይቶች መካሄዳቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ገልጸዋል።
"በውይይቱ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር የሃሳብ ልዩነት ቢኖርም እንኳ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰናል" ብልዋል።
በፌዴሬሽኑ መግለጫ መሰረት በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች በኔዘርላንድስ ሄንግሎ እ.አ.አ ሰኔ 8 ቀን 2021 የማጣሪያ ውድድር እንደሚያካሂዱ ተመላክቷል።
በሄንግሎ የማጣሪያ ውድድር የሚካፈሉት ከ800 እስከ 10 ሺህ ሜትር ርቀቶቸ የሚወዳደሩ አትሌቶች ናቸው።
በማጣሪያው የሚሳተፉት በዓለም የተሻለ ሠዓት ያላቸው፣ በ50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮና የተካፈሉ፣ ጥሩ ውጤት ያመጡና ሆቴል ገብተው ልምምድ እየሰሩ ያሉ ናቸው ተብሏል።
እንዲሁም በ50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮና በኮቪድና በጉዳት ምክንያት በማጣሪያው ያልተሳተፉ አትሌቶችም በሄንግሎ ማጣሪያ እንደሚካፈሉ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ ውጭ ያሉ አትሌቶች በራሳቸው ወጪ የቪዛ ሂደታቸውን ጨርሰው በሄንግሎ ማጣሪያ መካፈል እንደሚችሉና የተሻለ ውጤት ካመጡ እንደሚመረጡ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የፌዴሬሽኑ የሕክምና ክፍል ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት ጤና ሚኒስቴር፣ ኢንተርናሽል ክሊኒካል ላቦራቶሪስና አጋር አካላት እገዛ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
አትሌቶች በተለይ የዓለም የጤና ስጋት ለሆነው ኮቪድ-19 እንዳይጋለጡ አጋር አካላቱ ነጻ ምርመራ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎች እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።