የጊቤ 3 ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከፍተኛ የውሃ መጠን በመያዙ ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት ያስችለዋል -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የጊቤ 3 ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከፍተኛ የውሃ መጠን በመያዙ ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት ያስችለዋል -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
ግንቦት 3 ቀን 2013 (ኢዜአ) የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በወቅቱ ከሚጠበቀው መጠን ከስድስት ሜትር በላይ ውሃ መያዙ ተገለጸ።
ኃይል ማመንጫው አፍሪካን በኃይል በማስተሳሰር አንድ የኢኮኖሚ ቀጣና ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ እየተሰራ መሆኑንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።
የጊቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ንጉሴ ማሙሻ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ጣቢያው በዚህ ወቅት ከሚኖረው የውሃ መጠን ከአምናው ብልጫ ይዟል።
በዚህም የግድቡን የውሃ ከፍታ ከ862 ሜትር ወደ 868 እንዳሳደገው አስታውቀዋል።ይህም ከጣቢያው የሚመነጨውን ኃይል መጠን በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።
የግድቡ የውሃ መጠን በዚህ ወቅት መጨመር ሳይሆን፤ መቀነስ የሚያሳይበት እንደነበር የተናገሩት አቶ ንጉሴ፤ የዘንድሮው የውሃ መጠን ጭማሪ ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት ያስችላል ብለዋል።
በጣቢያው የገባው የውሃ መጠን ባለፉት አራት ዓመታት ከገባው በላይ ብልጫ እንደታየበትም አስረድተዋል።
ለአብነትም በ2008 የውሃው መጠን 819 ድረስ ወርዶ እንደነበር አብራርተዋል።
ጣቢያው ከፍተኛ የውሃ ሙሌት የነበረው ባለፈው ክረምት ወቅት የተመዘገበውም 892 ሜትር እንደነበር ያወሱት አቶ ንጉሴ፤ ከግድቡ አቅም በላይ በመሆኑ የግድቡን ደህንነት ለመጠበቅ ውሃ መለቀቁን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ለግድቡ ውሃ በሚመግቡ አካባቢዎች የሚታየው የአየር ሁኔታ የክረምቱ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያስከትል ተናግረዋል።
በመሆኑም በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነችና በኦሞራቴ ወረዳዎችና አካባቢያቸው የሚገኙ ነዋሪዎችና የስኳር ፋብሪካዎች ለጎርፍ አደጋ እንዳይጋለጡ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬሽን ፕላኒንግ ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲኣ እንደሚሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ወደ ስራ እስኪገባ ድረስ የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ለኢትዮጵያ የሃይል ፍላጎት ትልቁን ድርሻ የያዘ ነው።
ይህ ግድብ በዘንድሮ ዓመት በተለያየ መንገድ የዝናብ አማራጮችን ተጠቅሞ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ውሃ መያዝ እንዲችል መደረጉን ነው የገለፁት።
ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ውሃ መያዝ መቻሉ ለተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት ዓመታት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለደንበኞች መስጠት እንደሚያስችል ነው የገለፁት።
ግድቡ ሙሉ ለሙሉ መሙላቱ ከዚህ ቀደም ያገጠሙ የሀይል እጥረት ችግሮች እንዳይከሰቱ እና ዝናብ ባይዘንብና ለወደፊት ድርቅ እንኳን ቢያጋጥም እንደ ተጠባባቂ ሆኖ በማገልገል የኃይል መዋዠቅ እና መቆራረጥ እንዳይኖር ያደርጋል ነው ያሉት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጊቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከሚመነጨው ኃይል 400 ሜጋ ዋት ኃይል ለመሸጥ ወደ ኬኒያ የኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያና የማስተላለፊያ መሥመር ግንባታ እየተከናወነ ነው።
በኢትዮጵያ በኩል በወላይታ ሶዶ ከተማ የጣቢያው ግንባታና 446 ኪሎ ሜትር መሥመር ዝርጋታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የኢትዮ-ኬንያ ፓወር ሲስተም ኢንተርኮኔክሽን ፕሮጀክት ሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አያሌው ለኢዜአ አስረድተዋል።
ከኬንያ ወገንም ተመሳሳይ የኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያ በሱስዋ ከተማ ሆኖ የ600 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ 500 ኪሎ ቮልት መጠን ያለው ኃይል ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በማስተላለፍ የምሥራቅ
አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።
የጊቤ ሶስት የሀይል ማመንጫ ገና ሲጀመር የተለያዩ ጉዳዮች ይነሱበት የነበረ ቢሆንም አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ግን ከኢትዮጵያ አልፎ ምስራቅ አፍሪካ እና ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም የሃይል ትስስር በመሆን እያገለገለ ነው ይላሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬሽን ፕላኒንግ ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲኣ።
አፍሪካን በኃይል በማስተሳሰር አንድ የኢኮኖሚ ቀጣና ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ አስተዋጽኦ እንዳለው ጭምር ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ ከኃይል ሽያጭ ከምታገኘው ገቢ ባሻገር ጎረቤቶቿ የተሻለ ጥራት ያለው ሀይል እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ነው የገለፁት።
ግድቦችን ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር የቱሪስት መስህብ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል የገለጹት የስራ ኃላፊው ለኢትዮጵያ የሚፈለገውን ኃይል በማመንጨት የጎረቤት አገራትም ዘላቂ ኃይል በተፈለገው መጠንና ጊዜ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ነው የገለፁት።
መንግስት በኤሌክትሪክ ዘርፍ ሰፊ እገዛና ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በወላይታና በደቡብ ኦሞ ዞኖች የተገነባውና እውን እንዳይሆን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ሲደረግበት እንደቆየው የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከ2008 ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።