በርካታ የእስለምና እምነት ተካታዮች የታደሙበት የጋራ የአፍጥር መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በርካታ የእስለምና እምነት ተካታዮች የታደሙበት የጋራ የአፍጥር መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሄደ
ግንቦት 3 ቀን 2013 (ኢዜአ) በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ የእስለምና እምነት ተካታዮች የታደሙበት የጋራ የእፍጥር መርሃ ግብር የእምነቱ መሪዎችና ተከታዮች በተገኙበት ተከናውኗል።
በአዲስ አበባ 'ከሜክሲኮ እስከ ባምቢስ ባለው ስፍራ ነው የጋራ የጎዳና ላይ አፍጥር መርሃ ግብሩ የተከናወነው።
በመርሃ ግብሩ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ በዚህ ታላቁ የረመዳን ወር ይህን መሰል የአፍጥር መርሃ ግብር የሚገባ ነው ብለዋል።
መርሃ ግብሩ ለእምነቱ ተከታዮች አንድነት ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ያለው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅት ሕዝቡ ለአገራዊ እንድነቱ መትጋት እንዳለበት ያሳሰቡት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሁሉም እርስ በርስ በመደጋገፍና በመከባበር ሊኖር ይገባል ነው ያሉት።
ይህ ሲሆን የአገሪቱ ሰላም እየጠነከረ ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባት አገር መገንባት ይቻላል ነው ያሉት።
የመርሃ ግብሩ አዘጋጆችም ይህን የመሰለ ሁነት በማዘጋጀታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ከተማዋ ሁሉንም በእኩልነት የምታኖር መሆኗን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ አንዱ ለአንዱ ከለላና ሽፋን ሆኖ ሕዝቦች ተካበብረው የሚኖሩበት ከተማ ናት ያሉት አቶ ጃንጥራር የኢትዮጵያ ነጸብራቅ እንደመሆኗ ይህ ሁኔታ የሚያስቀናቸው አካላትን በጋራ ማሳፈር ይገባል በማለት ተናግረዋል።
ከእስልምና እምነት ተከታዮች ባሻገር ይህ መርሃ ግብር እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የክርስትና እምነት ተከታዮችም ምስጋና ያሻል ብለዋል አቶ ጃንጥራር።
የአፍጥር መርሃ ግብሩ ላይ የታደሙ የእስልምና እምነት ተከታዮችም መርሃ ግብሩ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
የእምነቱ ተከታዮች ኢትዮጵያ በርካታ የተለያዩ ማንነት ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት አገር እንደመሆኗ ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር እንደሚገባም ገልጸዋል።
1442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ከነገ በስቲያ ይከበራል።