ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዜጎች ጥላቻንና መቃቃርን ላለማውረስ በኃላፊነት ስሜት እንዲቀሳቀሱ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዜጎች ጥላቻንና መቃቃርን ላለማውረስ በኃላፊነት ስሜት እንዲቀሳቀሱ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 ለመጪው ትውልድ ፍቅርን ሰላምን አንድነትን እንጂ ጥላቻንና መቃቃርን ላለማውረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን አንገንባ" በሚል መሪ ሐሳብ ከሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኔሶታ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክተው ዛሬ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሰጡት መግለጫ ለመጪው ትውልድ ፍቅርን ሰላምንና አንድነትን እንጂ ጥላቻንና መቃቃርን ላለማውረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅት የታየው የለውጥ ጅማሮ እንዲቀጥልም ሁሉም ተደምሮ የፈረሰውን ግንብ ፍርስራሽ ቀስ በቀስ መጠራረግ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዶክተር አብይ ኢትዮጵያውያን በጋራ በአንድ አገር ጥላ ስር በፍቅር ይኖሩ ዘንድ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በመጨረሻም ዶክተር አብይ በአሜሪካ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር ገልጸው ለተደረገላቸው በፍቅር የተሞላ ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።