በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ጉዳይ ላይ ወደ አንድነት እንዲመጡ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ጉዳይ ላይ ወደ አንድነት እንዲመጡ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ጥሪ አቀረቡ
           አዲስ አበባ ግንቦት 03/2013 (ኢዜአ) በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ጉዳይ ላይ ወደ አንድነት እንዲመጡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ ብለዋል።
1ሺህ 442ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ጨረቃ መውጣት ላይ በመመስረት ነገ ረቡዕ ወይም ሐሙስ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል።
የኢድ በዓል ሲከበር ለድሆች ሰደቃ በማበርከት፣ ህሙማንን በመጠየቅና ከተቸገሩት ጋር አብሮ በመብላት ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት የኢድ በዓል በመስጊድ እንዲከበር መደረጉን አስታውሰዋል።
ዘንድሮ ደግሞ መንግስትና የጤና ባለሙያዎች በሰጡት መመሪያ መሰረት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከመስጊድ ውጭ በአደባባይ እንደሚከበር ነው የገለጹት።
የእምነቱ ተከታዮች ወደ ማክበሪያ ስፍራ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ በተገቢ የተክቢራና ሶላት ስርዓት ፈጽመው ወደየቤታቸው በመመለስ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን እንዲያሳዩ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሙስሊም የመከባበርና የሰላም ሰው መሆኑን የገለጹት ሐጂ ዑመር፣ ከተንኮል በመራቅ በሰላም አክብሮ መግባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች እንዳሉ አስታውሰው፣ ችግር ሲገጥም በሰላም እንዲፈታ ወደፈጣሪ መጸለይ እንደሚገባ ተናግረዋል።
"ከሱዳንና ግብጽ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ሌሎችን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ዳሩ ግን ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥ መታወቅ አለበት" ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ መደራደር እንደሌለባቸው ገልጸው፣ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ወገኖች በአገር ጉዳይ ላይ ወደአንድነት እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በመሆኑም ሰላምን በማጠናከር የአገሪቱ ልማት ከግብ እንዲደርስና አገራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ መከባበርና መተባበር እንደሚገባ ነው ሐጂ ዑመር የጠየቁት።
በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ የጎዳና ላይ አፍጥር ስርዓት እንደሚደረግ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
"እስከዛሬ በጎዳና ለተደረጉ የአፍጥር ስነ ስርዓቶች እኛ እውቅና አልነበረንም" ያሉት ሐጂ ዑመር፤ የዛሬው ግን በሰላም እንዲካሄድ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ስለመነጋጋራቸው ገልጸዋል።
ስርዓቱን ያዘጋጁ ወገኖችና የመንግስት ጸጥታ አካላት በሰላም እንዲጠናቀቅ በትብብር እንዲሰሩም አደራ ብለዋል።