ቀጥታ፡

የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን የሚታዘቡ ስድስት ባለሙያዎች ይልካል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት የምርጫውን ሂደት የሚታዘቡ ስድስት ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምንታዊ መግለጫው፤ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ከአውሮፓ ህብረት እና ከተለያዩ አገራት ባለሙያዎች እንደሚመጡ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚሁ ወቅት አንደገለጹት፤ ምርጫውን ለመታዘብ ከአውሮፓ ህብረት ስድስት ባለሙያዎች የሚመጡ ሲሆን ከአሜሪካና ከሩሲያም ተጨማሪ ባለሙያዎች እንደሚመጡ ገልጸዋል።

እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ቡድንም ምርጫውን ከሚታዘቡት መካከል መሆኑን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።

ከምርጫው ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ህብረት ቀደም ሲል ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ላይ በኢትዮጵያ በኩል የተደረገ የአቋም ለውጥ አለመኖሩን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።

በሳምንቱ በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር መገናኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።

ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር፣ ስለ ኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ ስለ መጪው አገራዊ ምርጫና ስለ አጠቃላይ የአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ገለጻ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረና ስትራቴጂክ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ግንኙነቱን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆየት እንደምትፈልግ ለልኡኩ መገለጹን አብራርተዋል።

በልዩ መልክተኛው በኩልም አሜሪካ የሶስትዮሽ ድርድሩ በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ፍላጎት ያላት መሆኑንና ተልዕኳቸውም ይህን ለማሳካት እንደሆነ መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞም የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ሲሼክዲ ከግብጽና ከሱዳን ጉብኝታቸው መልስ ትላንት ማታ አዲስ አበባ መግባታቸውን ይታወቃል።

አመጣጣታቸው የሶስትዮሽ ድርድሩን በማስቀጠል ሂደት ላይ ምክክር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘም በሳምንቱ የአፍሪካ ህብረት የቢሮ አባልና የኮሞሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዱዋሂር ዱካማል ኢትዮጵያ በመምጣት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተገኛኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በወቅታዊ የአገሪቷ ጉዳዮችና በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ማብራሪያ እንደተደረገላቸው ተጠቅሷል።

እንዲሁም በሳምንቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት ማድረጋቸውና ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ጋር መገናኘታቸው ይታወቃል።

በዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በቀጣዩ ምርጫ ፣ በህዳሴ ግድብና በትግራይ ክልል ስላሉ ወቅታዊ ጉዳዩች ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተገልጿል።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮች የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ፣ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩን አስመልክቶ እንዲሁም ስለ አገራዊው ምርጫው ባሉባቸው አገራት ላሉት የተለያዩ ባለስልጣናትና የሲቪክ ማህበራት ሲያስረዱ መቆየታቸውን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም