የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ
ጋምቤላ፤ ግንቦት 3/2013(ኢዜአ) የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና የብልጽግና ጉዞ በማስቀጠል የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።
ፓርቲው ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የምርጡኝ ቅስቀሳ በጎዳናና አደባባይ ላይ አካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት፤ ብልጽግና ሀገሪቱን እየተፈታተኑ ያሉትን የውጪና የውስጥ ጥላቶች በጋራ በመመከት የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ብሩህ ተስፋ ለማረጋገጥ ይሰራል።
ፓርቲው በህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት የኢትዮጵያ እድገትንና ብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋጥም ገልጸዋል።
ብልጽግና በመደመር እሳቤ ባለፉት ዓመታት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች በመጠበቅና ጉድለቶችን በማረም ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች ፓርቲ መሆኑም ተናግረዋል።
ፓርቲው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ለስኬታማነቱም መላው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ከምንጊዜውም በላይ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ የክልሉ ነዋሪዎች በቀሪዎቹ ቀናት ለመራጭነት የሚያበቃቸው ካርድ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው፤ ብልጽግና በብሄር ፣ በጎሳ ፣በቀለምና በቋንቋ ሳያደላ ሁሉንም እኩል የሚያገለግል፣ በህዝቦች መካከል አንድነትና ወንድማማችነት እንዲጎለብት የሚሰራ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው የህዝቦችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች በመፈጸምም ስራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድም ባለፉት ሶስታ ዓመታት የተሰሩት ምስክሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ነቅቶ በመመከት የጀመረነውን የስኬት ጉዞ እያስቀጠልን ነው ያሉት ኃላፊው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅም ፓርቲው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ ፓርቲው ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች ለመወዳደር ያቀረባቸውን ዕጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።