የመተከል ዞን ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና መውሰድ ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመተከል ዞን ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና መውሰድ ጀመሩ
ግንቦት 3/2013/ ኢዜአ/ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና መውሰድ ጀመሩ።
በስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት እና የክልሉ አመራሮች ተግኝተዋል።
ለ15 ቀናት የሚሰጠው የተሀድሶ ስልጠና ታጣቂዎች ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ ግንዛቤያቸውን በማስፋት ለአገርና ለአካባቢያቸው ጠቃሚ ዜጋ የሆነው እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ ነው።
በሥራ ፈጠራ ላይ ክህሎታቸውን ማሳደግ ሌላው የስልጠናው ዓላማ ሲሆን በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ማስቻልም የስልጠናው ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።
ታጣቂዎች በቆይታቸው ህገመንግስትና ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት፣ አገራዊ ለውጥ፣ ሥራ ፈጣሪነት፣ ወንጀል መከላከል፣ ሥነ ምግባር፣ ሥነልቦናና መሰል አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተመላክቷል።
የመከላከያ የስልጠና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ እንዳትለወጥ የሚፈልጉ ኃይሎች በአገሪቷ የእርስ በእርስ ግጭት በመፍጠር ለማትረፍ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
"ያለን አንድ አገር በመሆኑ ሁላችንም ሰላማችንን የመጠበቅ ሃላፊነት አለብን" ብለዋል።
ታጣቂዎችም የአገሪቱን ሰላም በማረጋገጡ ሂደት የድርሻቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል።
የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ዓለማየሁ ወልዴ በበኩላቸው ስልጠናው ታጣቂዎች ወደሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
"በክልሉ ከሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ያላቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና አለው" ብለዋል።
ይቅርታ በዜጎች መካከል ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ብርጋዲየር ጄኔራሉ፤ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት በሃይልና በግጭት ሳይሆን በመግባባት መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ብርጋዴር ጄኔራሉ ገለጻ ስልጠናው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያለው ድርሻ ትልቅ ከመሆኑ ባሻገር ለአካባቢውም ጥቅም መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።
የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት አማካሪ አቶ መንግሥቱ ቴሶ እንደተናገሩት፤ የተሃድሶ ስለጠናውን ለማስጀመር ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን መሆኑን ጠቁመው፣ ታጣቂዎች የልማት አቅም እንዲሆኑ የማስቻል ግብ እንዳለውም አብራርተዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዓለምነሽ ይባስ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ ከመከታታል ባለፈ ለአካባቢያቸው ሰላም ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ የእኔ ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል በሚል በሃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።