ትምህርት ሚኒስቴር ወላጆች እና መምህራንን የማመስገን መርሀ ግብር አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ትምህርት ሚኒስቴር ወላጆች እና መምህራንን የማመስገን መርሀ ግብር አካሄደ
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2013/ኢዜአ/ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች፤ መምህራኖቻቸውን እና ወላጆቻቸውን የማመስገን እና የማድነቅ ሀገር አቀፍ መርሀ-ግብር አካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መምህራኖች፣ ወላጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መርሀ ግብሩ ትምህርት ሚኒስቴር ከቅን ኢትዬጵያ ጋር በጋራ በመሆን የተዘጋጀ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የመመሰጋገን መርሀ ግብሩ የሚያመሰግን ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል።
መምህራን ትውልድን በመቅረፅ ከፍተኛ አስተዋጾ የሚያበረክቱ መሆናቸውን እና መምህርነት ትውልድን የምናነቃበት ሙያ በመሆኑ ምስጋና መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ወላጆች የነገ ትወልድን ከማፍራት አንፃር ላበረከቱት አስተዋጾ ማመስገን እንደሚገባ አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) ወላጆችን እና መምህራኖችን ማመስገን እና ማድነቅ ለከፈሉት መሰዎትነት እና ላመጡት ውጤት እውቅና መስጠት መሆኑን አስታውቀዋል።
በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር በቀጣይ አመት ወደ ተግባር በሚገባው በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የግብረ ገብ ትምህርት እንደሚሰጥት በኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለተግባራዊነቱም ወላጆች ፣ መምህራን እና ማህበረሰቡ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
መከባበር እና መደናነቅን በማስፋት መልካም ትውልድን ማፍራት ይገባ ያሉት ደግሞ የቅን ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ መሰለ ሀይሌ(ፒ ኤች ዲ) ናቸው።
ተማሪዎቹ በመምህራን እና ወላጆች የሚደረግላቸውን ድጋፍ በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አመለክተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተማሪዎቹ በበኩላቸው ለወላጆቻቸው እና ለመምህራኖቻቸው ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።
የምስጋና መርሀ ግብሩም በየአመቱ ግንቦት በገባ የመጀመሪያው ሳምንት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከበርምተገልጿል።