የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ
ግንቦት 3/2013(ኢዜአ) የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንደጠናቀቅና ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በርካታ የፀጥታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የዒድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዒድ አል-ፈጥር በዓል የእምነቱ ተከታዮች እርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት፣ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን የሚያዳብሩበት፣ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ተቻችለውና ተከባብረው በጋራ መኖርን ለመላው ዓለም የሚያሳዩበት በዓል መሆኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በርካታ የፀጥታ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በመላ ሀገሪቱ ያለው የክልልና የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ከሌሎች የፌዴራል ጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲከበር ኮሚሽኑ በቂ ዝግጅት በማድረግ የፖሊስ አባላትም በወትሮው ዝግጁነት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
«ኢስላም» እና «ሰላም» የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ መላው የሙስሊም እምነት ተከታዮች በዓሉ ያለምንም ፀጥታ ችግር እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንድያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በግዳጅና በኦፕሬሽን ላይ ላሉ የሰራዊቱ አባላት በሙሉ እንኳን ለዒድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።