ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ
ግንቦት 3/ 2013(ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ከሆኑት አምባሳደር ጀፈሪ ፈልትማን ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ና ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።
ውይይቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በመጪው 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ያተኮረ እንደነበረም ተገልጽል።
በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔዎች በተለይም ትግራይ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትንና መልሶ ማቋቋም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አካሄድ አብራርተዋል።
በተጨማሪም መጪው ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ስለተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እልባት እንዲያገኝ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት ለልዩ ልዑኩ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነትን በማንሳት፣ በሁለቱ አገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አምባሳደር ጀፈሪ ፈልትማን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፣ በሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል በሁሉም ተደራዳሪ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት በአገራቸው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ማረጋገጣቸውንም የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ቤ መረጃ ያሳያል።