ቀጥታ፡

1ሺህ 442ኛው የኢድ በዓል በአደባባይ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3/2013/ኢዜአ/ 1ሺህ 442 ኛው የኢድ በዓል በአደባባይ እንደሚከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ገለጹ።

ህዝበ ሙስሊሙ በበዓሉ የተቸገሩ ወገኖቹን በመደገፍ አብሮነቱን እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት የኢድ በዓል በመስጊድ እንዲከበር መደረጉን አስታውሰዋል።

ዘንድሮ መንግስትና የጤና ባለሙያዎች በሰጡት መመሪያ መሰረት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከመስጊድ ውጭ በአደባባይ እንደሚከበር ነው የገለጹት። 

በዓሉን በመከባበርና በሰላም ማክበር እንደሚገባ የተናገሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር፣ "ህዝበ ሙስሊሙ የተቸገሩ ወገኞችን በመደገፍ አብሮነቱን ሊያሳይ ይገባል" ብለዋል። 

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በሰላም አክብረው መመለስና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ማሳየት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። 


1ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ጨረቃ መውጣት ላይ በመመስረት ረቡዕ ወይም ሐሙስ ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል። 


ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር የዛሬው የአፍጥር ስነ ስርዓት በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ከከተማ አስተዳድሩ ጋር መወያየታቸውንም ገልፀዋል።

ስርዓቱን ያዘጋጁ ወገኖችና የመንግስት አካላት በሰላም እንዲጠናቀቅ ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር በመግለጫቸው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም