ቀጥታ፡

በወልድያ ከተማ የእስልምናና የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች የተሳተፉበት የጎዳና አፍጥር ስነ ስርአት ተካሄደ

ወልድያ ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) -በወልድያ ከተማ የእስልምናና የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች የተሳተፉበት የጎዳና ላይ አፍጥር ስነ ስርአት ትላንት ምሽት ተካሄደ።

በአፍጥር ስነ-ስርዓቱ ላይ  የዞኑ አስተዳዳሪ፣ የከተማው ከንቲባ፣ የወልድያ ከተማ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ሼህ ሀሰን ተማም የክርስትና ሀይማኖት ተከታይ ወጣቶች አካባቢውን በማጽዳትና ገንዘብ አሰባስበው የታሸገ ውሃና የምግብ ዝግጅት በማካሄዳቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ታዋቂው የሙስሊም አባት ሀጂ ሲራጅ አደም በበኩላቸው "የአፍጥር ዝግጅቱ በድህነት ላይ ያሉና  ተፈናቃይ ወገኖች የተሳተፉበት እንዲሁም ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ያጠናከረበት ነበር" ብለዋል።

"በዝግጅቱ ክርስቲያን ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸው ኢትዮጵያ ሁሉም ሃይማኖቶች ተሳስበውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ያስመሰከረ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው በሚካሄዱ የጋራ ልማቶች በንቃትና በጋራ ለመሰለፍ የተጀመረውን የትብብርና መረዳዳት መንፈስ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የወልድያ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ መላከ ብርሃን አክሊለ ብርሃን ተመስገን በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የነቢዩ መሃመድ ቤተሰቦችን በችግር ጊዜ ተቀብለው ማስተናገዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

"ይህ መልካም ጅምር ሁለቱ ሃይማኖቶች ተከባብረውና ተቻችለው እንደሚኖሩ ያሳየና መሰረት የጣለ ነው" ብለዋል ።

ኢትዮጵያዊ ሙስሊምና ክርስትያን ወንድሞች በሃይማኖት ቢለያዩም ሰው በመሆንና በጋራ ሀገራቸው አንድ መሆናቸውን ጠቅሰው መከባበሩ በጾም ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘወትር መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደ ትንሣኤ መኮንን በበኩላቸው አምልኮን በነፃነት ለመፈጸም በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ክርስቲያንና ሙስሊሙ የሀይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው የሀገራቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደ በፊቱ ሁሉ በጋራ እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም