ፕሮፌሰር ሰብሰቤ ደምሰው የ2021 የጆሴ ዋተርካሰስ የሀሩር አካባቢ የሥነ-እጽዋት ጥናት ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኑ

ግንቦት 2/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መስራች አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የ2021 የጆሴ ዋተርካሰስ የሀሩር አካባቢ የሥነ-እጽዋት ጥናት ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኑ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ለኢዜአ እንዳስታወቀው የአሜሪካው ስሚሶኒያን የተፈጥሮ ታሪክ ብሔራዊ ሙዚየም የእጽዋት ጥናት ትምህርት ክፍል ነው የዘርፉ ዓለም አቀፍ ተመራማሪ ለሆኑት ፕሮፌሰር ደምሴ ሽልማቱን ያበረከተላቸው።

ሽልማቱ በሙዚየሙ የእጽዋት ጥናት ትምህርት ክፍል እውቅ ተመራማሪና ሳይንቲስት በነበሩት ጆሴ ዋተርካሰስ ስም ነው እ.ኤ.አ ከ2001 ጀምሮ መሰጠት የተጀመረው።

የሽልማቱ ኮሚቴ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በሃሩራማ አካባቢ የእጽዋት ጥናት ዘርፍ በማስተማርና የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ማድረጋቸውን አረጋግጧል።

ጎን ለጎንም ፕሮፈሰር ሰብስቤ ለረጅም ዓመታት በዘርፉ አገር በቀል ብዝሃ ህይወት መረጃ በማሰባሰብና በመሰነድ ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸውን አስመልክቶ እውቅና ሰጥቷል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እጽዋቶችን፣ ፕሮጀክቶችንና የዘርፉን ብሔራዊ የሳይንሳዊ ጥናት እንቅስቃሴን በመምራት ረገድም ትልቅ ሥራ ሰርተዋል ብሏል ኮሚቴው።

ይህንንም ተከትሎ ስሚሶኒያን የተሰኘው የተፈጥሮ ታሪክ ብሔራዊ ሙዚየም ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴን በዘርፉ በአፍሪካ የሀሩር አካባቢ ሥነ-እጽዋት ጥናት ዘርፍ ላበረከቱተ አስተዋጽዖ እውቅና ሰጥቷቸዋል።

የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ በአሜሪካ ዋሺንግተን ከግንቦት 5 እስከ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው የስሚሶኒያን የሥነ-እጽዋት ጉባኤ ይካሄዳል ተብሏል።

ሽልማቱ የሚካሄደው የዘርፉን እውቅ ተመራማሪዎች ሥራዎችን ለማበረታታትና የሙዚየሙ እውቅ ሳይንቲስት የሆኑትን የጆሴ ዋተርካሰስ አሻራ ለማኖር ነው።

ፕሮፌሰር ሰብሰቤ ደምሰው የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የእጽዋትና የብዝሃ ህይወት ፕሮፌሰርም ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም