በአራት ዓመታት ለመትከል ከታቀደው 20 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ ዘጠኝ ቢሊዮኑ ተተክሏል-ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአራት ዓመታት ለመትከል ከታቀደው 20 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ ዘጠኝ ቢሊዮኑ ተተክሏል-ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02/2013 (ኢዜአ ) በአራት ዓመታት ለመትከል ከታቀደው 20 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ እስካሁን ዘጠኝ ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተመዘገቡ ውጤቶችና በቀጣይ በትኩረት በሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ዛሬ መክሯል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአካባቢ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ሥራዎች ተጠቃሽ ለውጦች መገኘታቸውን አስታውቋል።
የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በዚህ ወቅት እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም ህዝቡን በማሳተፍ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ዘጠኝ ቢሊዮን መትከል መቻሉን አስታውቀዋል።
"በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተተከሉ ችግኞችና የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎች የአገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል" ሲሉም ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ በመቋቋምና ምላሽ በመስጠት በኩልም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ነው ኮሚሽኑ የተናገሩት።
ለዚህም እስከ 2010 ዓ.ም ባለው አሃዝ መሰረት ከደን፣ ከግብርናና ከተለያዩ ዘርፎች 92 ነጥብ 6 ሜትሪክ ቶን ካርበን መቀነስ መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ፕሮፌሰር ፍቃዱ እንዳሉት ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደ የአፈፃፀም ጥናት መሰረት ከ2002 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ምላሽ ለመስጠት ከ82 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች ላይ በመሳተፍ ድምጿን ከማሰማት ባለፈ ጥሩ ውጤቶች መገኘታቸውንም ገልጸዋል።
"በጸደቀው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ እ ኤ አ በ2030 ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ልማት ተምሳሌት ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።
በተጨማሪም የአየርና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያግዙ የተለየዩ የህግ ማዕቀፎች ባለፉት ዓመታት ወጥተው ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን አመልክተዋል።
የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።
"የሬድ ፕላስ ፕሮግራም" አገር አቀፍ አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ በበኩላቸው "አገሪቱ ካላት የደን ሀብት ውስጥ ብዙም ተጠቃሚ አይደለችም ሲሉ" ይገልጻሉ።
የአገሪቱ 70 በመቶ መሬት ደን ለመትከል ምቹ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይ የደን ሽፋንን ለማሳደግ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሊጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
"በደን ልማት ላይ በትኩረት ካልተሰራ በአገሪቱ የውሃ ሀብት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል፤ ይህም በግድቦች፣ በመጠጥ ውሃና በእርሻ ላይ የራሱን ችግር ያስከትላል" ብለዋል።
በመሆኑም ያሉትን ደን ከመንከባከብ ባለፈ አዲስ ችግኝ የመትከሉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።