ወጣቶች ለሀገር ግንባታ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ማጎልበት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ለሀገር ግንባታ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ማጎልበት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ
ሀዋሳ ፤ግንቦት 2/2013( ኢዜአ ) ወጣቶችን በሁሉም መስክ በማሳተፍ ለሀገር ግንባታ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ማጎልበት እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።
"የወጣቶች ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ" በሚል ሀሳብ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ የተሳተፉት የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ እንዳሉት፤ወጣቶችን በሁሉም መስኮች ማሳተፍ ይገባል።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ወጣቱን በተገቢው መልኩ በፖለቲካው መስክ ማሳተፍ ባለመቻሉ ለግጭት እንዲጋለጥ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት በመቻሉ ለውጥ እንደመጣ ሁሉ በተመሳሳይ ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ ቢቻል አምራች ሀይል ለመፍጠር የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
በፖለቲካው ውሳኔ ሰጪነትና ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ወጣቱን ያማከለ እንዲሆኑ በማድረግ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የለውጥ ውጤቶች ውስጥ ወጣቱ ከማንም በላይ የጎላ ድርሻ እንደነበረው አስታውሰው በፖለቲካው መስክ ውሳኔ ሰጪ እንዲሆን ለማብቃት በምክር ቤት አባልነትና አመራርነት ጉልህ ስፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ በማህበራዊ የትስስር ገፆች በሚነዙ አፍራሽ ሀሳቦች ተጠምዶ ተገቢ ወዳልሆነ ድርጊት እያመራ ነው ብለዋል።
ይህ እንዲሆን ደሞ በሱ ትግል የተገኘውን ለውጥ እንደ ባይተዋር እንዲያ መደረጉ ነው ያሉት ዶክተር አያኖ ወጣቱ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል።
ወጣቱን በመልካም ስነ ምግባር የሚያንጽና ተገቢውን ዕውቀት እንዲያገኝ ለማድረግ መንግስት የትምህርት ስርዓቱን በማስተካከል ለለውጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምክንያታዊ፣ ሀገሩንና የሚወድና ሰርቶ በመለወጥ የሚያምን ወጣት መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በመረዳት ከቤተሰብ ጀምሮ መላው ህብረተሰብ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ለሀይማኖታቸው ያላቸው ቀናኢነት ወጣቱን በተገቢው መንገድ ለመምራት በሚውል መንገድ ሊጠቀሙበት ይገባል ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ዳኜ ሽብሩ ናቸው።
የእምነት ተቋማትና የሀይማኖት መሪዎች ለአምልኮ ስርዓት የሚመጣውን ወጣት ስነ ምግባር የተላበሰ እንዲሆን ማስተማር እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህርት ዳንሲታ አሰፋ በበኩላቸው፤ የነበረው የትምህርት ጥራት ችግር በወጣቱ የዛሬ ማንነት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
አሁን የተቀረጸው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ይህን ችግር ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመው፤ ሀገር በቀል እሴቶችን በማጎልበት ወጣቱን አሳታፊ የሆነ አሰራር በመከተል ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ፍቅር በህይወት የህጻናትና ወጣቶች የልማት ማህበር በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወጣት አብርሀም መሀሪ እንዳለው፤ በየአካባቢው የተገነቡት የወጣት ማዕከላት ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር በበቂ እየሰሩ አይደለም።
ማዕከላቱ በስነ ምግባር የታነጸ ወጣት ለማፍራት ትልቅ አቅም እንዳላቸው ቢታመንም በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ በተቃራኒ የሆኑበት ሁኔታ እንዳለ ተናግሯል።
ይህን ለማስተካከል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀላፊነት እንዳለበት በመረዳት ችግሩን ለመፍታት ወጣቱን ያሳተፈ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሀዋሳ አለም አቀፍ መነቃቃት አገልግሎት የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የወጣት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል።